፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 2 2016| NBC ETHIOPIA-የኢትዮጵያ 13ኛ ወር ጳጉሜን ቀናት ብሔራዊ ስያሜ ተሰጥቷቸው እየተከበሩ ነው። ጳጉሜ 2 የሪፎርም ቀን በአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን መሪነት “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺ አምላክ ገብረማርያምን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) ዓለም በምስቅልቅል ሂደት ውስጥ እያለፈ ሥልጣኔን እያረጋገጠ ጉዞውን መቀጠሉን ነው የገለጹት። ሥልጣኔን ለማረጋገጥ ምስቅልቅል ጉዞን ማለፍ ይጠይቃል ያሉት ዶክተር አህመዲን ኢትዮጵያም ሥልጣኔን ለማምጣት በምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ እያለፈች ለውጥ እያመጣች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ ስትገባ፣ የሰው ሃብት፣ ገበያ፣ መሬት፣ ኢነርጅ እና የተፈጥሮ ሃብት ላይ ያላትን ሃብት ይዛ መኾኑንም ተናግረዋል። እስካሁን ምን ተሠሩ ከዚህ በኋላስ ምን መሥራት ይገባል ብሎ መገምገም መጀመሩን ነው ያስታወሱት።
የተጀመሩ ውጤቶችን አጠናክሮ መቀጠል፣ ችግሮችን ማረም ያሰፈልጋል ያሉት ኀላፊው ችግሮችን ለመፍታት ሪፎርም ያሰፈልጋል ተብሎ እየተሠራ እንደኾነ ነው የተናገሩት። በመጀመሪያ የፖለቲካ ሪፎርም መካሄዱን ተናግረዋል። እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ለውጥ መደረጉንም አስታውቀዋል። በፖለቲካ በተሠራው ሪፎርም የብሔር ቅርጽ የነበራቸው ፓርቲዎች ውስጥ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ከፍ ማለታቸውን ገልጸዋል። የሚዲያ ሪፎርም መደረጉንም አመላክተዋል።

እንደ ሀገር ዘመኑን የሚመጥን የፖሊስ ሪፎርሞች መደረጋቸውንም ተናግረዋል። የሕግ ማዕቀፍ እና ፖሊሲዎች ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ወሳኝ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በተቋማት ላይ ሪፎርም መደረጉንም ተናግረዋል። በተቋማት ላይ ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞች መሠራታቸውን የተናገሩት ኃላፊው ለሥራ ምቹ ማድረግ እና ሌሎች ለውጦች መደረጋቸውን ነው የገለጹት።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት እና ኢንሳ ሪፎርም የተደረገባቸው ናቸው ብለዋል። የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በለውጡ የተወለደ የሀገር ኩራት የኾነ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። የኢኮኖሚ ሪፎርም መደረጉንም ተናግረዋል። በኢኮኖሚ የተሠራው ሪፎርም ወደ ቁልቁለት ሲሄድ የነበረውን ኢኮኖሚ ማሻሻል እና መለወጥ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

ስብራቶችን ለመጠገን ሪፎርም መደረጉን ነው የገለጹት። ለነዋሪዎች የምንሰጠው አገልግሎት መሻሻል እና መጠገን ይገባዋልም ብለዋል። ለላቀ አገልግሎት መትጋት እና መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። አገልግሎት መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። በአማራ ክልል በሪፎርም ለውጥ ያመጡ ሥራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው በክልሉ ለውጥ ያልመጣባቸውን ጉዳዮች ለውጥ እንዲያመጡ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት ዘገባው የአሚኮ ነው፡፡












