፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 1 2016| NBC ETHIOPIA- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየደረጃዉ ላሉ የፍ/ቤት አመራሮች፣ ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች በአዳዲስ ፖሊሲዎች ፤ የሕግ ጉዳዮች ፤ የዳኝነት አመራር እና የፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በዛሬው መድረክም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2016 ዓ.ም መተግበር በጀመረው የፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዙሩያ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩም የፌደራል ፤ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ምርጥ ተሞክሮ፣ የሦስቱም ፍ/ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ አመት የትኩረት መስኮች ቀርበዉ የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል፡፡

የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከአዝጋሚና በቁጥቁጥ ከሚደረግ መጠነኛ ለዉጥና የማሻሻያ ሥራ በተለየ መልኩ ፍርድ ቤቶች ነፃ፤ ቀልጣፋ ፤ውጤታማ እና ተደራሽ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉበት ቁመና ላይ ለማድረስ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱና መዋቅራዊ አደረጃጀቱን ሥር ነቀል በሆነ መንገድና ከመሰረቱ የሚቀይሩበትና የሚመሩበት እቅድ ነው ሲሉ የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓለምአንተ አግደው ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም ይህ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተሟላና አዲስ እይታን መሰረት በማድረግ እምርታዊ ለዉጥ የሚመዘገብበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች አሁን ካላቸው አቋም በሁሉም ረገድ የተሻሉ ማድረግ የትራንስፎርሜሽን እቅድ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ተናግረዋል፡፡
ጠንካራ የፍትህና የዳኝነት ሥርዓት በሀገሪቱ ለመገንባት የዳኝነት ስርዓቱን ዘመናዊ፤ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በማድረግ እና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠይቅ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ ለማድረግም አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ቀልጣፋ ማድረግ ላይ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በ-ሰላማዊት ወ/ገሪማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












