፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 1 2016| NBC ETHIOPIA- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ በርካታና ውስብስብ ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግባለች ሲሉ ተናገሩ።
ጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሀሳብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እና ሌሎች የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም እየተከበረ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ሩቅ ዓልማና መልካም ራዕይን ሰንቃ በቀየሰችው የእድገትና ብልፅግና ጉዞ በግስጋሴ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር በርካታና ውስብስብ ፈተናዎችን በመቋቋም አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበችም ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሀገርን በድል ማስቀጠል የተቻለበት ሂደት ጠቃሚ ተሞክሮዎች የተገኙበትና ለቀጣይ የእድገት ጉዟችን እንደወረት የሚወሰድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ከምትታወቅበት የስንዴ ልመና ወጥታ የውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ስንዴ ለውጭ ገበያ መላክ ወደቻለችበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሸጋገሯን አንስተዋል።
በስንዴ ልማት የታየው ለውጥ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የአርሶ አደሩን ህይወት በማሻሻል፣ የግብርና ኢኮኖሚውን በማጎልበትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ጉልህ ድርሻን ያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደተሟላ የማምረት እንቅስቃሴ በማስገባትና አቅማቸውን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ረገድ እመርታዊ ሽግግር መደረጉንም ገልጸዋል።ይህም ትምህርት የሚወሰድበትና ላስቀመጥነው ሀገራዊ ራዕይ ስንቅ ሆኖ የሚያለግል ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉ ተወዳዳሪነት እንዲጠናከር፣ የኤክስፖርት ንግድ እንዲስፋፋ፣ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ እንዲሁም በርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያስቻለ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበትና የትውልዱ የቃልኪዳን ሃውልት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሰራርና የአመራር ውስንነት ምክንያት ተንገራግጮ ከቆመበት በብልህና ቆራጥ አመራርና ውሳኔ ሃይል ወደ ማመንጨት በማሸጋገር የሉአላዊነታችን መገለጫ አንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ የመንግስት ቀዳሚ የትኩረት መስክ በማድረግ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሃገርና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን በማልማት የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ፀጋ ወደሚመጥን የቱሪዝም መዳረሻነት ተሸጋግረናል ብለዋል።
በተለያዩ የልማት መስኮች የተጀመረ ሰፋፊ ስራዎችና የተገኙ ድሎች የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ትክክለኛነት እና የሀገራዊ ብልፅግና ፍኖት የኢትዮጵያን ራዕይ እንደሚያሳካ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።
ካለፉት ፈታኝ ጉዞዎች ትምህርቶችንና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለቀጣይ ድሎች መታጠቅና ተስፋን መሰነቅ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ በጎ ጅማሮ የሚበሰርበትና አዲስ ምዕራፍ የሚታወጅበት እንደመሆኑ መጠን መንግስትና ህዝብ በታደሰ ቁርጠኝነትና በጠነከረ የትብብር መንፈስ ለላቀ ስኬትና ድል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ስለሆነም በተገኙ ድሎች ሳንኩራራና በሚገጥሙን ፈታናዎች ሳንደናቀፍ በጀመርነው የእድገትና ብልፅግና ሂደት በፍጥነት በመጓዝ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሁሉም ሀገርንና ህዝብን በቅንነት፣ በታታሪነትና በፍፁም ቁርጠኝነት ማገልገልና ለላቀ ሀገራዊ ድል መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገትና የብልፅግና ጉዞ እንዲሁም በተለያዩ የልማት መስኮች እያደረገች ያለችውን ተስፋ ሰጪ ሽግግር ለማሳካት ጉልህ ሚና ለተጫወቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












