፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 20 2016| NBC ETHIOPIA- የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለ2017 የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ለማስተማር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎችን በክልሉ ለማስተማር ታቅዶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጳጉሜ አራት ቀን ድረስ የትምህርት ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑን አመላክተዋል:: የአማራ ክልል ከነበረበት የፀጥታ ችግር አኳያ የትምህርት ሒደት መስተጓጎል መከሰቱን ጠቁመው፤ በተለየ ሁኔታ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ምዝገባና የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች ቀድሞ አካሂዷል ብለዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችን ለመመዝገብ መድረኮችን የማዘጋጀት እንዲሁም ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በሁሉም የክልሉ ዞኖች የተማሪ ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችሉ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው የትምህርት ዘመን የመጽሐፍት እጥረት እንደነበር አቶ ጌታቸው አንስተው፤ የአምናውን ጨምሮ 14 ሚሊዮን መጽሐፍት ታትመው እየተሰራጩ መሆኑንና ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ተብሎ ባይታመንም ከአምናው በተሻለ ተደራሽ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
ክልሉ መጽሐፍትን ለማሳተም አንድ ቢሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተው፤ የታተሙ መጽሐፍትን ከማጓጓዝ አኳያ ግን አንዳንድ የፀጥታ ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሩን በመቋቋም ለትምህርት ቤቶች ለማድረስ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በክረምቱ የትምህርትን ስትራቴጂካዊ ችግሮችንና ወቅታዊ ችግሮችን የለየ ዕቅድን አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጉን አንስተዋል።የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት ሥራን ለመሥራት ፈታኝ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ሲያስተምር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ትምህርት ከማንኛውም የፖለቲካ እሳቤ ነፃ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ትምህርት በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ምሑራን እንዲሁም ከክልሉ ውጪ ያሉ ግለሰቦችና የተለያዩ አካላት አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።መንግሥት ትምህርት ቤቶች በተሻለ ሁኔታ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ጥረት እያደረገ መሆኑ ጠቅሰው፤ ነፍጥ ያነገቡ አካላት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች እህትና ወንድሞቻቸው መሆናቸውን ተረድተው ሕፃናቱ የትምህርት እድሜያቸው እንዳይባክን ሠላም መፍጠር እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።












