በባልካን ባህረ ገብ መሬት ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ግሪክ በሰሜን ምዕራብ ከአልባኒያ፣ በሰሜን ከመቄዶንያና ቡልጋሪያ፣ በምስራቅ ከቱርክ ጋር ድንበር ትጋራለች።
131,957 km2 በሚሸፋነው መሬቷ ከ10 ሚሊየን በላይ ህዝብ ይኖርባታል።የጥንት ግሪክ ሥልጣኔ በ1200 ዓ.ዓ ገደማ ካበቃው ከመይሴኒያ ሥልጣኔ እስከ ታላቁ እስክንድር የስልጣን ዘመን ማብቂያ 323 ዓ.ዓ. እንደሚደርስ ይነገራል።
ዓለም ዛሬም በዘርፉ የምትጠቀምባቸው በፖለቲካ፣በፍልስፍና፣ በኪነጥበብ እና በሳይንስ የተመዘገቡት ዘመን የማይሽራቸው ውጤቶች የጥንታዊ ግሪክ ሥልጣኔ መለያናቸው፡፡
በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጥንታዊ ግሪክ ደራሲ ሆሜር አንስቶ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮማግዛት እስከ ወደቀበት ድረስ ያለው ትልቁ ታሪካዊ ወቅት ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ያጠመረ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
በስልጣኔ፣ በፖለቲካ፣ በኪነጥበብ ፣በሳይንስ እና በፍልስፍና ፈርቀዳጅ የሆነችው ግሪክ በወቅተ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በስፋት የሚካሄዱባት ሀገር ጭምር ነበረች፡፡በጥንቷ የግሪክ ደቡባዊት ክፍል ኦሎምፒያ እ.ኤ.አ በ776 የተካሄዱ ጨዋታዎች አለም አሁንም ድረስ በጉጉት የሚጠብቀውን እና በ የ4ዓመቱ የሚዘጋጀው የኦሎምፒክ ውድድር መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል፡፡
አሁን ድረስ ኦሎምፒክ በመባል የሚታወቀው ስፓርታዊውድድር የመጠሪያ ስሙንም ያገኝው ግሪክ ውስጥ ከሚገኝው የኦሎምፒያ ተራራ ነው።የዘመናዊው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መስራች የሆነው ፈረንሳዊው ባሮን ፒየር ደ ኩበርቲን ነበር።
ባሮን በ393 ዓ.ም በኦሎምፒያ ግሪክ በተካሄደው እና በርካታ ይዘት ባላቸውጥንታዊ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በመማረክ ሀገራት ውድድር ለማዘጋጀት የሚፎከከሩበትን የዛሬውን የኦሎምፒክ ጨዋታለዓለም ህዝብ አስተዋውቋል፡፡

የኦሎምፒክ ውድድር መስራች የሆነቸው ግሪክ የሠረገላ ውድድር፣ የፈረስ እሽቅድምድም፣ ሩጫ፣ ነፃ ትግል፣ ፔንታሎን እና ቦክስ በጊዜው ከተለመዱ የስፖርት ውድድሮች ቀዳሚዎቹ ነበሩ።
እ.ኤ.አ በ1896 የመጀመሪያው እና ዘመናዊውየኦሎምፒክ ጨዋታ በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ነበርየተካሄደው፡፡ግሪኮች በቀደመው የአውሮፓ ታሪክ ላይ በፍልስፍና፣ በሂሳብ፣በሥነ ፈለግ ጥናት( አስትሮኖሚ) እና በሕክምና ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል።
ሥነ ጽሑፍ እና ቴያትር የግሪክ ባህል የጎላ ገጽታ ሲሆን ለዘመናዊ ድራማ መጀመር ተጽዕኖው የጎላ ነበር፡፡ግሪኮች በተራቀቁ ሀውልቶቻቸው እና የህንፃ ጥበባቸው ይታወቃሉ። ሶቅራጥስ፣ ፕላቶ እና አርስቶትል የመሳሰሉ ታዋቂ ፈላስፎች መፍለቂያቸው ግሪክ ነው፡፡ግሪክ በኦሎምፒክ ጀማሪነቷ እና በጥንት ስልጣኔዋ ለአለምካበረከተችው ትሩፋቶቿ ባለፈ ሃገሪቷ ሊጎበኙ በሚችሉ አስደናቂ ቦታዎች የተሞላች ናት፡፡
ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ይተማሉ፡፡ ከመዲናዋ አቴንስ ጀምሮ እስከ 11 ካሬ ማይል ስፋት እስካላት የሃሊኪ ደሴት በርካትየቱሪስት መዳረሻዎች ይገኛሉ፡፡ያልተለመደ ስነ-ህንፃ ዲዛይን ያለው የቻኒያ ከተማ የግሪክ አንዱ መገለጫ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የሆሊዉድፊልሞች እና ተከታታይ የቲቪ ድራማዎች መቼት በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
ሳንቶሪኒ የተሰኘው ከተማ ደግሞ በኖራ በተለበጡ ህንፃዎች፣ለአይን በሚስቡ ትንንሽ ቀለማት ያሸበረቁ ቤቶች፣ጠመዝማዛ መንገዶች እና ከፍ ያሉ ጉልላቶች የተገነቡበትነው፡፡ ስፍራው ያለው እይታ እና ማራኪ ስነ-ህንፃ ዲዛይን የቱሪስትን ቀልብ ይስባል፡፡በግሪክ የሚኖአን ሥልጣኔ መነሻዋ የኖሶስ ከተማ በብዙዎችዘንድ በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከተማ እንደሆነች ይነገራል፡፡

በውስጧ የያዘቻቸው ታሪካዊ እና ጥንታዊ ስፍራዎች ልዩ ያደርጋታል፡፡ ከተማዋ በሄራክሊዮን ዳርቻ ላይ የምትገኝ ሲሆን ታዋቂየቱሪስት መዳረሻ ሆና አመታትን ተሻግራለች፡፡የአስደናቂው የኖሶስ ቤተ-መንግስት ቅሪቶች የዚያን ጊዜ አስደናቂዊ ስነ-ህንፃ ዲዛይን ክህሎት ማስረጃዎች ናቸው።በተጨማሪም በሄራክሊን በሚገኘው የአርኪኦሎጂ ሙዚየም በጥንታዊ ግሪካዊያን ሲገለገሉባቸው የነበሩ የተለያዩ ዕቃዎችን እና ምስሎችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ስፍራን አካቶ የያዘ ነው፡፡
ከነዚህ ከተሞች በተጨማሪ የማይኮኖስ ባህር ዳርቻ፣በናፍፕሊዮ ያሉ የቬኒስ አርክቴክቸር፣ የኦቶማን አወቃቀሮች፣የጥንት ግድግዳዎች፣የመካከለኛው ዘመን ሐውልቶች እንዲሁም የዴልፊ ከተማ ባለው ጥንታዊነት እና ታሪካዊነቱ በዩኔስኮ መዘገብ ላይ ሊሰፈር ችሏል፡፡
በ- ዮርዳኖስ አባይነህ












