፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 14 2016| NBC ETHIOPIA-የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከክልሉ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እና ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት አድርጓል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት የዳኝነት አገልግሎቱን ፈጣን እና ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የማሻሻያ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ላይም ተቋሙ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ መድረሱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ፍ/ቤቶችን በቴክኖሎጅ የማዘመን ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ መዝገብ ለማስከፈት ከሩቅ ቦታዎች የሚደረግ ጉዞ ቀርቶ ተገልጋዮች በአቅራቢያቸዉ በሚገኙ ፍ/ቤቶች (ማዕከል) አስከፍተዉ መዝገቡ በቴክኖሎጅ ወደሚፈለገዉ ፍ/ቤት የሚደርሰበት አሰራር ይፈጠራል።
በተመሳሳይ ለክርክር ከተለያየ ቦታ ፍ/ቤቶች ወዳሉበት የሚደረግ ረጅም ጉዞ እና እንግልት ቀርቶ ተከራካሪዎች በአቅራቢያቸዉ ባለ ፍ/ቤት በሚደራጅ ስማርት ኮርት በቴክኖሎጅ ታዘዉ ክርክር የሚያደርጉበት ሁኔታ ይመቻቻል።
ተከራካሪዎች ጉዳያቸዉ የደረሰበትን ደረጃ በእጅ ስላካቸዉ ላይ በሚኖር መተግበሪያ መከታተል ሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። የዉሳኔ ግልባጭ ለመዉሰድ ወራት ይወስድ የነበረዉ ጊዜ ድምጽን ወደያዉ ወደ ጽሑፍ በሚቀይር ቴክኖሎጅ በመታገዝ ዉሳኔዎችን ወዲያዉ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

መዛግብት ስካን ተደርገዉ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ በቴክኖሎጅ ስለሚያዙ ዳኞች መዝገብ እየተሸከሙ ሚሄዱበትንና መዛግብት ሕንጻ የሚያጨናንቁበትን ሁኔታ ይቀይራል።በስምምነቱ መሰረትም ከየተቋማቱ የተሰየሙ ባለሙያዎችና አመራሮች ያሉበት የቴክኒክና አብይ ኮሚቴ ተደራጅቶ ስራ እንደሚጀምር ገልፀዋል።
የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) አዲሱ የጥቅላይ ፍርድቤት የጀመሩት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አድንቀው የክልሉ ምክርቤት እና ቋሚ ኮሚቴ ከጎናችሁ በመሆን እንደግፋለን ብለዋል።
የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የቻለ ይግዛው እንዳሉት የክልሉን ፍላጎት መሸከም የሚችል የቴክኖሎጂ ተቋም መገንባት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችል የሰው ኀይል ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በኮሚሽኑ እየለሙ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ባላቸው ተቋማት ላይ እንዲተገበሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንዱ በመኾኑ ተቋሙን ለማዘመን ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ.ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን ከ300 በላይ ስምምነቶችን ከውጭ ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ተፈራርሞ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ የሚኾኑት ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት መቻሉን አንስተዋል። አሁንም ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ እንዲኾን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ዩኒቨርሲቲው እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እና አገልግሎቶችን ጥራት ባለው መንገድ እና በአጭር ጊዜ ለመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ተቋማቱን በአዳዲስ አሠራሮች ወይም በቴክኖሎጂ ማጠናከር አንዱ ተግባር መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እንዲሁም የምርምር ተቋማት ቀዳሚውን ድርሻ ወስደው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
📌YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
📌 TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
📌Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
📌Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












