፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 19 2016| NBC ETHIOPIA- ከቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በርካታ አማራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የዜና ሰአታቸውን ዘለግ በማድረግ ብቅ ማለት ችለዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በአለማችን በሚገኙ ሁሉም ሀገራት የየራሳቸው ዜና ነጋሪ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሏቸው ሲሆን አንዳንደዶቹ ከሀገራቸው አልፈው በመላው አለም አማራጭ የዜና ምንጭ ለመሆን በቅተዋል፡፡
ለዛሬ በአለማችን ከፍተኛ ተመልካች ካፈሩ አለም አቀፍ የቴሌቪዥን የዜና ቻናሎች መካከል ጥቂቶቹን እንንገራችሁ፡፡
ኬብል ኒውስ ኔትወርክ ወይም ሲኤንኤን

በሰኔ ወር በፈረንጆቹ 1980 የመጀመሪያው 24 ሰአት የዜና ቻናል በመሆን ነበር ስራውን የጀመረው፡፡ መቀመጫውን በሀገረ አሜሪካ አትላንታ ያደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያው በንግግር ስራ በተሰማራው ቴድ ተርነር አማካኝነት እንደተገኘም ይነገርለታል፡፡
በጄፍ ዙከር የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና መቀመጫው በተመሰረተበት አትላንታ ነው፡፡
ሴ ኤን ኤን በ36 የዓለም ሀገራት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከ 4000 በላይ ሰራተኞችም አሉት፤ የቴሌቪዥን ቻናሉ በ24 ሰአት ውስጥ የሚከወኑ ሁነቶችን በዜና ለተመልካቾቹ የሚያደርስ ሲሆን በፈረንጆቹ 2021 በተሰራ ጥናት በተመልካቾችም ምርጫም የ3ኝነት ደረጃን ይዘዋል፡፡
ስካይ ኒውስ

በስካይ ግሩፕ ባለቤትነት የተያዘ ብሪቲሽ የዜና የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡
በ1989 በወርሃ የካቲት ስራውን የጀመረው የቴሌቪዥን ጣቢያው የራዲዮ ጣቢያም አለው፡፡
በጆን ራይሌ የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያው በፈረንጆቹ 2000 ነበር የ24 ሰአት የዜና አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡በፎክስ ግሩፕ ኔትወርክ አማካኝነት ለመላው አለም የሚደርሰው የዜና ቻናሉ በመላው አለም ከ18 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተመልካቾች እንዳሉት ይነገራል፡፡
ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ ፤ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለዜና በሚሆን መልኩ በማዋቀር በ24 ሰአት የአየር ላይ ቆይታው ለተመልካቾቹ ያደርሳል፡፡
ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ)

በ1936 በህዳር 14 ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው ቢቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስራውን የጀመረው በሬዲዮ ሞገድ በ1922 ነበር፡፡
በእንግሊዝ ለንደን ዋና መቀመጫውን ያደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያው በየዕለቱ በአጠቃላይ የ120 ሰአት የዜና ስርጭት በሬዲዮ፤ ቴሌቪዥን እና ኢንተርኔት አማረጮች ይዞ ይቀርባል፡፡
በ6ቱ አህጉራት ከ38 ሺ በላይ ሰራተኞች ያሉት የቴሌቭዥን ጣቢያው የአለማችን ግዙፉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ነው፡፡ በመላው አለም በ24 ሰአት ውስጥ የሚከወኑ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳይ ስፖርትን ጨምሮ የሚዳስሱ ዜናዎችን ለተለመልካቾቹ ያደርሳል፡፡ ከ426 ሚሊየን በላይ ተመልካች ያለው የዜና ቴሌቪዥን ነው፡፡
ኤም ኤስ ኤንቢሲ

በአሜሪካን ኒውዮርክ መቀመጫውን ያደረገ የዜና ቻናል ነው፤ በኤንቢሲ ኒውስ ግሩፕ ባለቤትነት የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያው በፈረንጆቹ 1996 ነበር ወደ አየር ላይ ብቅ ያለው፡፡
ዋና መቀመጫው ሴውካውሲ ኒውጀርዚ ሲሆን በአሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ተመልካች ካላቸው የዜና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡
ከአንድ ነጥብ 2 አምስት ሚሊዮን በላይ ቋሚ ተመልካች ያሉት የቴሌቪዥን ጣቢያው በይበልጥ በአሜሪካ የሚከወኑ ሁነቶች ላይ የ24 ሰአት የዜና ሽፋን ይሰጣል፡፡
ኤፍ ኤን ሲ ወይንም ፎክስ ኒውስ

በፈረንጆቹ 1996 በጥቅምት ወር ፎክስ ኮርፖሬሽን ባለቤትነት የተጀመረ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡
በቀጥታ ስርጭት ለ15 ሰአታት የሚተላለፈው ወቅታዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዜናዎችን ለተመልካቾቹ ያደርሳል፡፡ በ86 ሀገራት የሚታየው ቴሌቭዥን ጣቢያው በዋነኝነት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለተመልካቾቹ ይደርሳል፡፡ በአሜሪካ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች አሉት፡፡
በ- የአብስራ ሚሊዮን












