፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 13 2016| NBC ETHIOPIA- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሃገር ክብር የላቀ ገቢ ለአዲስ አበባ ብልፅግና” ንቅናቄ የ2016 በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና የ2017 ማስጀመሪያ እየተከናወነ ይገኛል።
ሙስና እና ብልሹ አሰራር ዘርፉን እየፈተነው መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አደም ኑሪ ይህም ቢሮው በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ እየጎዳው ነው ብለዋል።
የሙያ ስነምግባር ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉ 89 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።
ቢሮው በሂደት የሚሰበስበው ገቢ መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን በእዚህም ባለፋት ሁለት ዓመታት የ35% ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
በመጀመሪያው የ2015ቱ “ግብር ለሃገር ክብር የላቀ ገቢ ለአዲስ አበባ ብልፅግና” ንቅናቄ 108 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ዛሬ ማጠቃለያ በሚያገኘው የ2016ቱ ንቅናቄ 146.9 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተነግሯል።
ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም ማደግና ጠንካራ የገቢ ተኮር ክትትልና ድጋፍ ለገቢው መጨመር ከምክንያቶቹ መካከል ናቸው ተብሏል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አበቤ መዲናዋ ከነዋሪዎቿ በሰበሰበችው ገቢ የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ የኮሪደር ልማት፣ የኑሮ ማቅለያ የገበያ ማዕከላትን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሰርታበታለች ብለዋል።
ከተማዋ ከፍተኛ ገቢ የማመንጨት አቅም እንዳላት ያነሱት ከንቲባዋ የተገኘው ገቢ መልካም ቢሆንም ከእዚህ በላይ ይጠበቃል ሲሉ አደራ ሰጥተዋል።
በመርሃ ግብሩ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ክፍፍልና የስራ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል። በበጀት ዓመቱ 230 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል።
በመርሃ ግብሩ በዘርፉ ጥሩ አፈፃፀም አስመዝግበዋል የተባሉ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች እና የነጋዴ ማህበር አመራሮች ተገኝተውበታል።
በ-መቅደስ ደምስ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












