፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 05 2016| NBC ETHIOPIA- በአለም ላይ ግዙፍ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅቶች መካከል ሳምሰንግ ከፊት ይቀመጣል፡፡
ሳምሰንግ የዓለማችን ትልቁ የሜሞሪ ቺፕስ፣ ስማርት ስልኮችና ቴሌቪዥኖች አምራች ድርጅት ነው። ሳምሰንግ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ገበያው የተቀላቀለው በአውሮፓውያኖቹ 1969 ሲሆን የመጀመሪያ ምርቶቹም ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥኖችን ናቸው፡፡
አሁን ላይ ደቡብ ኮሪያ በአጠቃላይ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ አንድ አምስተኛ ያህሉን የሚሸፍነው ይህ ድርጅት ለመሆን በቅቷል፡፡ሳምሰንግ ግሩፕ ዋና መቀመጫውን በደቡብ ኮሪያ ሲኦል ያደረገ ሲሆን በ74 አገሮች ውስጥ ቅርንጫፎችን በመክፈት ከ270 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድልን መፍጠር ችሏል፡፡
ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ድርጅት ሳምሰንግ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጉ ሞባይሎችን በመሸጥ ከ30 ትሪሊየን የኮሪያ ዋን በላይ ገቢ ይሰበስባል፡፡ይሁን እንጂ ድርጅቱ በ2023 ከ196 ቢሊየን ዶላር በላይ አመታዊ ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን ካለፈው አመት 2022 ጋር ሲነጻጸር የ15 ነጥብ 6 በመቶ የገቢ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ይህ ድርጅት ነው ታዲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት የሚገኙት፡፡ከነዚህ ፈተናዎች መካከል ዋነኛው ከሰራተኞቹ እየገጠመው የሚገኝ ተቃውሞ ሲሆን ከደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በደቡብ ኮሪያ የቴክኖሎጂ አምራች ግዙፉ ኩባንያ ሳምሰንግ የሰራተኞች ማህበር ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ አባላቶቹን ላልተወሰነ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ህብረቱ ውሳኔውን ያሳለፈው የድርጅቱ የስራ ሀላፊዎች ባቀረበው ጥያቄ ላይ ለመነጋገር ፍላጎት ባለማሳየታቸው ነው የተባለ ሲሆን አድማው ለሶስት ቀናት ይቆያል ተብሏል፡፡
በደቡብ ኮሪያ ውስጥ አንድ አራተኛውን የሳምሰንግ ሰራተኞችን የሚወክለው ብሔራዊ ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ህብረት NSEU የስራ ማቆም አድማው የተቋሙን የምርት ሂደት እንዳስተጓለው ተናግሯል።
ሳምሰንግ በበኩሉ በምርቶቹ ላይ ምንም አይነት እክል እንዳልገጠመው ገልጾ ተከራክሯል፡፡ ኩባንያው አክሎም ከህብረቱ ጋር በቅን ልቦና ድርድር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
ሆኖም ህብረቱ “ሳምሰንግ ከመጀመሪያው አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ በኋላም ቢሆን የመነጋገር ፍላጎት ስለሌለው ከሀምሌ 10 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ሁለተኛውን አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ እናውጃለን” ሲል የተቋሙን የእንነጋገር ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡
ብሔራዊ ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ህብረት NSEU እስካሁን 6 ሺህ 500 የሚጠጉ ሰራተኞች በአድማው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጾ በርካታ አባላቱ አድማውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።
የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ቃል አቀባይ ምን ያህል ሰራተኞች የእግር ጉዞውን እንደተቀላቀሉ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።ሰኞ እለት በተካሄደው ተቃውሞ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል ተብሏል፡፡ የሰራተኞች ህብረቱ ከተመሰረተ ከረጅም አመታት በኋላ ባለፈው ወር የመጀመሪያውን የተቃውሞ የእግር ጉዞ ማድረጉ ይታወሳል፡፡












