፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 27 2016| NBC ETHIOPIA-የዓለም መንግስታት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የ91 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል ይላል የሲኤን ኤን የፊት ለፊት ዘገባ፡፡ ከጠቅላላው የዓለም ኢኮኖሚ ጋር የተጠጋጋው ገንዘቡ የበርካታ የዓለም ሀገራትን ጀርባን ያጎበጠ ነውም ይላል፣ በተለይም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት ያወጡት ወጪ ልዕለ ሃያላኑ ሀገራትን ሳይቀር ኪሳቸውን አራቁቷል፤ ኢኮኖሚያቸውን አናግቷል፣ የኢኮኖሚ የበላይናተቸውን አስቀጥሎ የመሄድ ህልውናቸውን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡
ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የሚጠበቁት የአመታዊ በጀት ጉድለቶች እና እያሻቀበ የሚገኘው ዕዳ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ የዕዳው በከፍተኛ መጠን ማሻቀብ መንግስታትና ባለሀብቶችን እንቅልፍ ነስቷቸዋል፡፡
ሀገራት ያለባቸው እዳ እያሻቀበ በመጣ ቁጥር ለመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎት የሚመድቡት ወጪ እንዲያንስ ከፍ ሲል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት፣ ወረርሽኝ፣ ብሎም ጦርነት ቢገጥማቸው ለምላሽ የሚሆን ኢኮኖሚያዊ አቅም ያሳጣቸዋል፡፡ የኑሮ ጫናውን መቋቋም ያቃታቸው ዜጎችና ንግዶች ለተጨማሪ ብድር መጋለጣቸው የሀገራቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ይጎዳል፡፡ የተጠራቀሙ እዳዎች ወለድ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የግል ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ ብሎም መንግስታት ከሚያጋጥሟቸው ኢኮኖሚያዊ ውድቀቶች ለማገገም ብድር እንዳያገኙ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል፡፡
አንዲት ሀገር እዳዋ ምን ያክል ሲደርስ ነው ብዙ የሚባለው ሲል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን የጠየቀው ሲ.ኤን.ኤን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ ከ150 በመቶ ሲሻገር የሚል ምላሽን አግኝቷል፡፡ ብዙ ከመባል አልፎ ስጋት ሊባል ይችላል ነው የተባለው፡፡

ዕዳ “ከእንግዲህ ነፃ አይደለም” ይላሉ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰሩ Kenneth Rogoff፡፡ በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር በሁለት ሺ አስራዎቹ በርካቶች የብድር ወለዶች ለዘለዓለም ነጻ ሆነው እንዳሻቸው ያለሀሳብ እንደሚበደሩ ያስቡ ነበር የሚሉት ባለሙያው ያ ታሪክ ሆኗል ሲሉ ሁኔታውን ያብራራሉ፡፡ በመላው ዓለም እየሆነ ያለውም ያ ነው ባይ ናቸው።
የአሜሪካ መንግስትና ባለሃብቶቿ ላለፉት ዓመታት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ትልቅ የራስ ምታት ሆኖባቸው ሰንብቷል፡፡ ከእዚህ ጋር በተገናኛ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ. ኤም.ኤፍ ባሳለፍነው ሳምንት ሀገሪቱ ላለባት የረጅም ጊዜ ዓመታዊ በጀት ጉድለቶች በአስቸኳይ መፍትሄ ልትሰጣቸው ይገባል በሚል ዳግም ማስጠንቀቂያ ሰንዝሯል፡፡
እ.ኤ.አ በግንቦት 2024 የሀገሪቱ የህዝብ ዕዳ ወደ 34 ነጥብ 55 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ መድረሱን የስታትስቲክ መረጃ ያሳያል፡፡ በ2024 ብቻ የእዚህ ገንዘብ 892 ቢሊዮን ዶላር ወለድ ክፍያ ይጠበቃል፡፡ ገንዘቡ ሲሰላ ሀገሪቱ ለመከላከያዋ ከመደበችው በጀት በላይ ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመት ይህ መጠን አንድ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚሻገር የአሜሪካን የኮንግረሱ የበጀት ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፡፡
በ2025 ደግሞ ዕዳው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 166 በመቶውን ሊይዝ እንደሚችል ትንበያውን ያስቀመጠው ቢሮው ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደኋላ እንደሚጎትተው አሳስቧል፡፡በመላው ዓለም በርካታ ምርጫዎች እየተካሄዱ ቢሆንም ባለስልጣናት ችግሩን ችላ በማለት ከታክስ ጭማሬና የወጪ ቅነሳ ጋር በተያያዘ የብድር ማዕበሉን ለመቋቋም ከተቻለም ለመግታት ተሰፋ ካደረገው መራጩ ህዝብ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሽ የዋጋ ግሽበትን ሊያስከትሉና አዳዲስ ቀውሶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ ተስፋዎችን እየሰጡ ነው በሚል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እየተቹ ነው፡፡
አሜሪካ የዕዳ ክምሯ እየጨመረ ስጋቷ ቢያይልም በመጪው በፈረንጆቹ ህዳር 5 ለምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋነኞቹ እጩዎች ጆ ባይደንም ሆኑ ዶናልድ ትራምፕ ለጉዳዩ ትኩረት እየሰጡ አይደሉም በሚል ትችት እየተሰነዘረባቸው ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በሲ.ኤን.ኤን ቴሌቭዥን በተላለፈው የፕሬዚዳንትነት ክርክር ሁለቱ ግለሰቦች አንዳቸው ሌለኛቸውን የሀገሪቱን የዕዳ ሁኔታ አባብሰሃል በሚል ተካሰዋል፡፡ ተመሳሳይ ችግርን እያሳለፈች የምትገኛውና በጎርጎሮሳውያኑ 2023/24 መገባደጃ ላይ የመንግስት ሴክተር የተጣራ ዕዳዋ ሶስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የተሻገረው ዩናይትድ ኪንግደም በነገው እለት የምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማው ላይ ቢገኝም ፖለቲከኞቿ በጉዳዩ ዙሪያ ዝምታን መርጠዋል፡፡የፊስካል ጥናት ኢንስቲትዩትም ሀገሪቱ እዳዋ ከሀገር ውስጥ ምርቷ 98 በመቶ ያህሉን ቢደርስም ሁለቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመረጡትን ዝምታ ክፉኛ አውግዟል።
በተመሳሳይ ጀርመን የዕዳዋን ጉዳይ ለመፍታት ፈታኝ ትግል ውስጥ ገብታለች፡፡ አስተዳዳሪዎቿ ከፍተኛ የውስጥ ሽኩቻ ውስጥ የገቡ ሲሆን ጉዳዩ በተያዘው ወር ዋነኛ የፖለቲካ ጡዘት መንሰኤ እንዳይሆን ተሰግቷል፡፡
በታህሳስ 2023 እዳዋ 3430 ቢሊዮን ዶላር የተሻገረው ፈረንሣይ ያለባት ብድር ከውጥረት ባሻገር ለከፍተኛ ፖለቲካዊ ውዥንብር ዳርጓታል፡፡ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ወር አስቸኳይ ምርጫ ከጠሩ በኋላ በሀገሪቱ የፋይናንስ ቀውስ ስጋት አሳሳቢ ሆኗል። ህዝቡ የሀገሪቱን ከፍተኛ የብድር እና የበጀት ጉድለት ያባብሳል ያሉት የቀኝ ዘመሙን ናሽናል ራሊ ፓርቲ እንዳይመርጥ ብዙዎች ስጋት ገብቷቸዋል፡፡
የዓለም መንግስታት የ91 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ በመላው ዓለም ዜጎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው እንደሚበረታ እየተነገረ ነው፡፡ ለችግሩ እልባት ለመስጠት የዓለም መንግስታት ቢከብዳቸውም ከባድ የሚባሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ የግድ እንደሚላቸው የተሰጠ ጥቆማ ነው፡፡












