፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 19 2016| NBC ETHIOPIA- እ.ኤ.አ በ2006 ለተመልካቾች የቀረበ ፊልም ነው፡፡ በላሪ ቻርልስ ዳይሬክት የተደረገ ሲሆን ባሮን ኮሄን ዋና ገጸ ባህሪውን በመላበስ ተውኖበታል፡፡መቼቱን በካዛኪስታን እና አሜሪካ ያደረገው ፊልሙ ለተመልካቾች እይታ ከቀረበ በኋላ ተዋናዩ በሚያሳያቸው ያልተለመዱ ተግባራት ሳቢያ በብዙ የካዛኪስታን ነዋሪዎችና መንግስት ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ኋላም የተወደደ አወዛጋቢ ፊልም ነበር- ቦራት
የኮሜዲ ዘውግ ያለው ፊልሙ በካዛኪስታን የመረጃ ሚኒስቴር ጋዜጠኛ ሆኖ እያገለገ በሚገኘው ቦራት ስራው በፈጠረለት አዲስ አጋጣሚ የሚገጥመዉን ውጣ ውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ቦራት ስለ አሜሪካ ባህል፣የአኗኗር ዘዬ እንዲሁም እንዴት ታላቅ እና ሀያል የኢኮኖሚ ባለቤት እንደሆነች በማጥናት ዶክመንተሪ ለመስራት ከካዛኪስታን ወደ አሜሪካ ሲያቀና የሚያሳይ ፊልም ነው፡፡ጋዜጠኛው እንግዳ በሆነበት ሀገር የመጣበትን አላማ ከግብ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት፣ በመንገዱ ከሚገጥሙት ሰዎች ጋር ለመግባባት የሚፈጥረው መስተጋብር እና ፓሜላ አንደርሰን ከተባለች ተዋናይት ጋር በፍቅር ለመጣመር የሚጓዝባቸውን ውስብስብ መንገዶችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ቦራት ከሀገሩ ባህል እና ወግ ውጪ የአሜሪካውያን የሚከተሉትን ልምዶች በመመሳሰል ሲያከናውቸው እንዲሁም ያልተለመዱ ተግባራትን በሀገሪቷ በተዘዋወረበት ስፍራዎች ሁሉ ሲያከናውን ፊልሙ ያሳያል፡፡
ቦራት 20th Century Fox እ.ኤ.አ ነሐሴ 4 2006 በአሜሪካ ትራቨርስ ከተማ ለእይታ የቀረበ ሲሆን ህዳር 2 እና 3 በአሜሪካ እና እንግሊዝ ፊልሙ መታየት ጀምሯል፡፡ ፊልሙ 18 ሚሊየን ብር ወጪ ሲደረገበት በብዙዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ በመሆን ከወጣበት ወጪ 18 እጥፍ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት ችሏል፡፡በዓለም ዙሪያ ባገኘው አድናቆት እና ተወዳጅነትም ፊልሙ 262 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡
ቦራት ፊልም ለተመልካቾች እይታ ከቀረበ በኋላ ተዋናዩ በሚያሳያቸው ያልተለመዱ ተግባራት ሳቢያ በብዙ የካዛኪስታን ነዋሪዎች እና መንግስት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ከዛም አልፎ ተርፎ የካዛኪስታን መንግስት በሁሉም የአረብ ሀገራት ፊልሙ እንዳይታይ ያሳገደ ሲሆን ክስ ሊመሰረትበትም ችሏል፡፡ ከበርካታ ውዝግብ በኋላ እ.ኤ.አ መስከረም 2020 ቦራት ቁጥር ሁለት በምስጢር ተቀርጾ መጠናቀቁ ተሰማ፡፡ ከአንድ ወር በኋላም ጥቅምት 23 በአማዞን ስቱዲዮ ተለቋል።

የቦራት የመጀመሪያ ፊልም በሀገሪቱ ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ ቀጣዩ የፊልሙ ክፍል ለእይታ ሲቀርብ የሀገሪቱ የቱሪዝም ቦርድ ቦራትን ወሳኝ የቱሪዝም መሳቢያ መንገድ በማድረግ ይጠቀመው ጀመር፡፡
የሀገሪቱን ባህል፣ ወግ፣የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች፣ ጥንታዊ ስፍራዎችን የታደለችው ካዛኪስታንን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ እንደ ልዪ አጋጣሚ ተጠቀሙበት፡፡ የሀገሪቱ የቱሪዝም ቦርድ በሚያሰሯቸው በርካታ አጫጭር ማስታወቂያዎች ቦራት በፊልሙ በተደጋጋሚ የሚጠቀማትን “በጣም ጥሩ” የምትለውን ስንኝ በማካተት ማስተዋወቁን ተያያዙት፡፡ በዚህም ሀገሪቷ ለመጎብኘት የሚመጡ አለም አቀፍ ቱሪስቶች መበራከት ጀመሩ፡፡
የአለም ባንክ ግሩፕ ይፋ ባደረገው መረጃ እ.ኤ.አ. በ 2005 4ሚሊየን 365ሺ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ለመዝናኛ እና ለበዓላት ለመታደም ሀገሪቷን መዳረሻቸው ማድረጋቸውን ያመላክታል፡፡ የቦራት ፊልም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እይታን እና ተወዳጅነትን ካገኘ በኃላ ካዛኪስታንን የሚጎበኙ ቱሪስቶች መጨመሩን የአለም ባንክ ግሩፕ ሪፖርት ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2023 ወደ ካዛክስታን የተጓዙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር 9.2 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
በፊልሙ በመሪ ገጸባህሪነት የተወነው ባሮን ኮሄን የGolden Globe የሽልማት ውድድር ላይ Best Actor in a Motion Picture– Musical or Comedy በመባል የተሸለመ ሲሆን Academy Award for Best Adapted Screenplay ዕጩ መሆን ችሏል፡፡












