፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 14 2016| NBC ETHIOPIA- በአማራ ክልል ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የሚገመግም መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ መድረኩ የዞኖችና የከተማ አስተዳደሮችን እንዲደግፉ የተላኩ የድጋፍና ክትትል ቡድኖች ሪፖርት ላይ ውይይት በማካሄድ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ነው።
በየአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማነትን በማስቀጠልና ችግሮችን ለይቶ በመፍታት የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያመቻች ገልጸዋል።

የክልሉን ህዝብ ችግሮች ለመፍታት ባለን አቅም ልክ በቁርጠኝነት መስራት ይጠይቃል ብለዋል። በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አባላት የአካባቢውን ጸጋ በመለየትና የህዝብን ፍላጎት በማገናዘብ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በመድረኩ ዞኖችንና የከተማ አስተዳደሮችን እንዲደግፉ ስምሪት የተሰጣቸው ቡድኖች የሚያቀርቡትን ሪፖርት ከመገምገም ባሻገር የመንግስት ስራዎች እንደሚታዩ ገልጸዋል።
የክልሉ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፤ እርሳቸው በተሳተፉበት በጎንደርና አካባቢው ህዝቡ ሰላምን በማስፈንና የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።በተለይም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ህዝቡ በራሱ አደረጃጀት በመፍጠር እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ በምልከታቸው መገንዘባቸውን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ንጹህ ሽፈራው፤ እርሳቸው በተሳተፉበት በደብረ ብርሃንና አካባቢው ህዝቡ መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ ይፈልጋል ብለዋል።
የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠትና የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ህዝቡ የድርሻውን እንደሚወጣ በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይና ሌሎች ከፍተኛ የአመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












