፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 30 2016| NBC ETHIOPIA-በጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችው ወረራ ዓለምን በሁለት ጎራ አሰልፎ እስከዛሬ እያከራከረ ነው፡፡ ወረራውን በመቃወም በርካታ ምዕራባውያን የክሬምሊን አቅም ለማዳከም ያለሙ ለቁጥር የሚዳግቱ እገዳዎችን ጥለውባታል፡፡ የነዳጅ ሽያጭና ከሀገር ውጪ ያሏት ንብረቶች ገደቦች ተጥለውባቸው፣ በርካታ ምዕራባውያን ኩባንያዎች ከሩሲያ ገበያ ወጥተው ከተቀሩት የዓለም ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ትስስር ቀዝቅዟል፡፡
ጦርነቱ ተጀምሮ ማዕቀቦች መጉረፍ ሲጀምሩ የምዕራባውያን ባለስልጣናት እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሩሲያ ኢኮኖሚ ማንሰራራት እንዳይችል ሆኖ እንደሚሽመደመድና ታይቶ ለማይታወቅ ውድቀት እንደሚዳረግ ሲናገሩ ነበር፡፡ ሀገሪቱ እነኚህን ግፊቶች የምትቋቋምበት አንዳች ሃይል እንደማይኖራት በእርግጠኝነት የሚናገሩ ነበሩ፡፡
በጎርጎሮሳውያኑ 2022 ታህሳስ ላይ የአውሮፓ ህብረት እና ቡድን ሰባት ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን ነዳጅ አንዱ በርሜል ከ60 ዶላር በታች እንዲሆን በማድረግ የምታገኘውን ገቢ ለመቀነስ ያለመ የዋጋ ማሻሻያ አድርገው ነበር፡፡
ኢኮኖሚዋ ሲንኮታኮት ጦሯን ወደነበረበት ትመልሳለች ተብላ የተጠበቀችው ሩሲያ ግን ከዓላማዋ ሳትዛነፍ ጦርነቱን ቀጥላ ሃያ ስምንተኛ ወሩን ይዛለች፡፡ ለውድቀት የታጨው ኢኮኖሚዋ በእድገት ጎዳና እየገሰገሰ ትንበያዎቹን ፉርሽ እያደረገ ነው፡፡
ማዕቀብ የተጣለባት ሀገር ሚዛኗን የምታጣው አማራጭ እስክታገኝ፣ ምርቶቿን የምትሸጥባቸው ሌሎች ገበያዎች እስክታመቻች ድረስ ስለመሆኑ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ከሆነ ሩሲያም አሁን ላይ ከባዱን ጊዜ አልፋ የተረጋጋችበት ወቅት ነው፡፡

በምዕራባውያን ገደቦች ይሽመደመዳል የተባለው ኢኮኖሚዋ ባልተጠበቀ መልኩ በደቡብና ምስራቅ የዓለም ክፍል አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እየፈጠረ ብዙዎችን እያስደመመ ነው፡፡ ወደአውሮፓ የነበረውን የነዳጅ ሽያጯን ወደህንድና ቻይና አዙራለች፡፡
ቻይና የሩሲያ ቀዳሚ የነዳጅ ዘይት መዳረሻ በመሆን የኢኮኖሚዋ ህልውና መሰረት ሆና የትስስር ገመዳቸው ጠብቋል፡፡ ባለፈው ዓመት የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ 240 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ ክብረወሰን ሆኗል፡፡
ከነዳጁ በዘለለ በሩሲያ ከተሞች የኤሌክትሮኒክስ መደብሮች በቻይና ቁሳቁሶች የተሞሉ ሆነዋል፣ የተሸከርካሪ መሸጫዎቿ በአብላጫው በቻይናውያን የመኪና ነጋዴዎች ተይዘዋል፡፡ ሩሲያ ሰራሹ ቮልጋ መኪና በቻይናው ቻንጋን መኪና አይነት ተሰርቶ ለገበያ ቀርቦም ነበር፡፡
እርምጃቸው ያሰቡትን ውጤት አለማጣቱንና ሀገሪቱ በቀላሉ መሰናክሉን ማለፍ መቻሏን ራሳቸው ምዕራባውያን አልሸሸጉም፡፡ እርምጃቸው መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በዓለም የነዳጅ ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ማሻቀብን ማስከተሉን የተረዱት እኚህ አካላት ውሳኔያቸውን ቆም ብለው እንዲያስቡበት አስገድዷቸዋል፡፡
ሞስኮ ዛሬም ገቢዋን እየሰበሰበች በዩክሬን ምድር ለምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ የሚያስፈልጋትን ወጪ እየሸፈነች ነው፡፡
የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም ዛሬም ድረስ ማዕቀቦቹ ሱቆቿን አላራቆተውም፣ የገበያ ማዕከሎቿን አላቀዛቀዛቸውም፡፡ የማዕቀብ ጣዮቹ ሀገራት ምርቶች በአንአድም ይሁን በሌላ መንገድ ወደሩሲያ ግዛት መግባታቸው አልቀረም፡፡
የአውሮፓና አሜሪካ ኩባንያዎች ሀላፊዎች ኢኮኖሚያዊ ዝግጅቶችን ለመታደም ወደሩሲያ እግራቸው ላይረግጥ ይችላል፡፡ በሩሲያ መንግስት አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው በአንድ ወቅት የሩሲያው ዳቮስ በሚል ይጠራ በነበረው የሴንት ፒተርስበርግ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ፎረም ላይ መታደም ግን የግድ ይላቸዋል፡፡ ከትላንትና ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት መካሄድ የጀመረው የ27ኛው የሴንት ፒተርስበርግ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመታደም ከ136 ሃገራት 17 ሺኅ በላይ የመንግስት እና የንግድ ተወካዮች ሩሲያ ገብተዋል፡፡

የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ.ኤም.ኤፍ በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 ከየትኛውም የዓለም ሀገር በሚልቅ መጠን የ3.2% ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደምታስመዘግብ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
ሩሲያ ገቢዋ ባይስተጓጎልም ከምንም ቅድሚያና ዳጎስ ያለውን ፈሰስ የምታደርገው የጦር ሃይሏ ላይ ሆኗል፡፡ በእዚህም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ የወደፊት እጣፋንታ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ እንዳያልፍ ስጋት የገባቸው ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡
ሞስኮ በጎርጎሮሳውያኑ 2020 መሰረተ ልማት፣ መጓጓዣና ለመሳሰሉት ብሄራዊ ፕሮጀክቶች 400 ቢሊዮን ዶላር መድባ እንደነበር የሚገልጹ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሁን ላይ ይህ ገንዘብ ለወታደራዊ ኢንዱስትሪው እየዋለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በሚሰሩ ዓለም ዓቀፍ ባንኮች ላይ የሁለተኛ ደረጃ ማዕቀቦችን እጥላለሁ በማለት እያስፈራራቸው ነው፡፡ ይህም ሩሲያን ለአዲስ ችግር እንዳይዳርጋት ስጋት ፈጥሯል፡፡












