፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት29 2016| NBC ETHIOPIA-የነገስታት ምድር ይሏታል ባላት በርካታ የቱሪስት መዳረሻ እና በቀለማት ባሸበረቀ የኪነ ህንጻ ጥበቧ የበርካታ አለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ የቻለች ናት የህንዷ ራጃስታን ፡፡
በህንድ ሰሜን ምዕራብ ግዛት የምትገኘው ራጃስታን በህንድ ከሚገኙ ግዛቶች ትልቋ ናት ፡፡ ባላት የባህላዊ መስህቦቿ እና ታዋቂ ሆቴሎቿ በተለይም በአሜሪካ ጎብኚዎች ዘንድ ተወዳጅነት እና እውቅናን ማትረፍ ችላለች፡፡
በተለያዩ ቀለማት የተሽቆጠቆጡ ‹‹ ከለር ኮድ ሲቲ›› የተሰኙ በቀለም ያሸበረቁ ከተሞቿ በብዙዎች ዘንድ እንድትታወቅ አድርገዋታል፡፡
እ.ኤ.አ በ1799 የተገነባው ሃዋ ማሃል ቤተመንግስት ለከተማዋ እንደምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ቤተመንግስቱ በየዘመኑ የነበረው የኪነ ህንጻ ጥበብ የታየበት እና ያልተለመደ ቅርጽ ያለው ነው፡፡ ይህ የፒራሚድ ቅርጽ ያለው ህንጻው አምስት ወለሎች እና 953 መስኮቶች አሉት ፡፡ ይህም የዘመኑ ሴት የንጉሣዊያን ቤተሰቦች በከተማዋ የሚካሄዱትን ሁነቶችን በነፃነት መመልከት እንዲያስችላቸው ታስቦ የተገነባ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ውጫዊ ገጽታው ወደ ፒንክ ቀለም ያደላ በመሆኑ ለከተማዋ ‹‹ፒንክ ከተማ›› የሚል ቅጽል አስገኝቶላታል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ መዝገብ ላይም መስፈር ችሏል ፡፡

ጆድፑር ወይም ሰማያዊ ከተማ ራጃስታን ግዛት ውስጥ የምትገኘው ይቺ ከተማ በርካታ ቤቶቹዋ ሰማያዊ ቀለምን የተላበሱ በመሆናቸው ስያሜውን እንድታገኝ አድርጓታል ፡፡ ከከፍታ ላይ ሆኖ ለሚመለከተው ሰውም የተለየ አስደሳች እያታን ይፈጥራል ፡፡
ራጃስታን ከቻይናው ትልቁ ግንብ ቀጥሎ የአለማችን ሁለተኛው ረጀሙ የኩምባልጋር ግንብ መገኛም ናት፡፡ በተራራ ጫፍ ላይ 1100 ሜትር ከፍ ቦሎ የተሰራው ግንቡ 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው ፡፡ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባ ሲሆን በዩኔስኮ የአለም ቅርጽ መዝገብ ላይም ሰፍሯል ፡፡
ሌላኛው ለጉብኝት ወደ ራጃስታን ያቀና ሳይመለከተው የማይመለሰው ታሪካዊቷን ኔምራና ከተማን ነው ፡፡ ከተማዋ በተለየ ባህል፣ በታሪክ እና በስነ ህንጻ ጥበብ የበለጸገች እንደሆነች ይነገርላታል ፡፡ ወደ ከተማዋ የገባ ጎብኚም ግርማ ሞገስ የተላበሰውን የኔምራና ፎርት ቤተ መንግስትን መጎብኘት ፣ በተፈጥሮ ፍልውሃዎች መዝናናት እንዲሁም ጥንታዊ ቤተመቅደሶችን መጎብኘት ሊዝናናባቸው ከሚችላቸው ነገሮች መካከል ናቸው ፡፡
በዓለም ላይ ትልቁ የግመል ትርኢት ወይም ‹‹የፑሽካር ፌር›› በዝችው ግዛት በፑሽካር ከተማ በየዓመቱ ይካሄዳል ፡፡ በፌስቲቫሉ ደማቅ የባህል ትርኢቶች ፣ የእንስሳት ንግድ ፣ ሃይማኖታዊ ስርአቶች ይከወኑበታል፡፡ በርካታ አለም አቀፍ ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች በሺህ የሚቆጠሩ ግመሎች ሲያጌጡ፣ሲሽቀዳደሙ እና ሲሸጡ ለመመልከት ከየአቅጣጫው ይጎርፋሉ ፡፡

ከዚህም በተጨማሪም የህንድን የተለያየ ታሪክ የሚያሳዩ ስምንት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ስፍራዎች የሚገኙበት መሆኗ ራጃስታን ልዩ መልኳ ነው ፡፡
በእነዚህ እና ሌሎች በተሸለመቻቸው ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶቿ ራጃስታን ከ2024 ምርጥ የጉዞ መዳረሻዎች አንዷ መሆን ችላለች ፡፡
በ- የአብስራ ብርሃኑ












