፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 26 2016| NBC ETHIOPIA- ኤንቢሲ ኢትዮጵያ በምክክሩ ሊነሱ ይገባቸዋል በሚሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችን አወያይቷል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ሃገራዊ ምክክር እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲቀርቡ መቆየታቸውን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ሃገሪቱ ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ምክክርን የግድ የሚል ስለመሆኑ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

ምክክሩ ዘግይቷል የሚሉት ፓርቲዎቹ ይህም ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት አንስተዋል፡፡ ብሄራዊ መግባባት ሊደረስባቸው ይገባል ባሏቸው እንደ ባንዲራ፣ ብሄራዊ መዝሙር፣ የወሰን ማካለል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አወቃቀር፣ የምርጫ ስርዓት፣ የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት ያሉ ጉዳዮች በዋናነት ወደ ጠረጴዛ መምጣት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ቅይጥ ማንነት ወይም ብሄረሰባዊ ማንነት በምክክሩ ሊካተት ይገባል የተባለ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቅይጥ ማንነት (ብሄረሰባዊ ማንነት) የታደለች ብትሆንም እንደ ጥሩ እድል የፖለቲካ ሃይል ጥቅም ላይ አልዋለም ተብሏል፡፡

ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚገዳደሩበትና የሚወቃቀሱበት ሳይሆን ለምክክሩ መሳካት የድርሻቸውን የሚያዋጡበት ሊሆን እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡
በምክክሩ ሁሉም ሃሳብ ይገዛል ማለት እንዳልሆነ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን የሚሳተፉ አካላት ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑም ጥሪ ቀርቧል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ለምክክሩ መሳካት የበኩላቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባልም ተብሏል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ሂደት አዲስ አበባን ቅድሚያ አድርጎ የምክክር ምዕራፉን ጀምሯል፡፡ ካሳለፍነው ግንቦት 21 ጀምሮ እየተደረገ በሚገኘው የአዲስ አበባው የምክክር ምዕራፍ የተለያዩ የህብረተሰቡን ክፍል ወክለው በመጡ አስራ አንድ ተወካዮች አማካኝነት ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል የተባሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በነገው ዕለትም መቋጫውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በ-መቅደስ ደምስ
????YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
???? TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
????Website – https://nbcethiopia.com/news/
????Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












