፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 21 2016| NBC ETHIOPIA-የጤና ሚኒስቴር የጤና ግብአቶችን እና መገልገያ መሳርያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረትና የዜጎችን የተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሟላት እንደዚሁም የሀገሪቷን ዕድገት ለማፋጠን በዘርፉ የተሰማሩቱን የመደገፍ እና የማጠናከር ስራዎችን ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ይህንን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ የመጀመሪያውን የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ሀገርአቀፍ ኤግዚቢሽንን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የገለፀ ሲሆን ጉዳዩ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ከሚገኙ ሀገራዊ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው በተለያዩ ዘርፎች በአምራችነት የተሰማሩትን ሀገር በቀል አምራቾች በመደገፍ እና በማበረታታት እንደዚሁም አዳዲስ አምራቾችን ወደ ዘርፉ በመቀላቀል የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ በመሆኑ የጤና ሚኒስቴርም በዘርፉ የበኩሉን ሚና ለመጫወት ያለመ ኤግዝቢሽን ማዘጋጀቱን ተናግሯል።
ኤግዚብሽኑ ከ150 በላይ አምራቾች ይሳተፉበታል የተባለ ሲሆን አቅራቢዎችና አምራቾች ትስስር የሚፈጥሩበት፣ የዉጭ ኢንቨትመንትን ለመሳብ እንዲሁም እንደሀገር ያሉ አቅሞችን ለመፈተሽ ያግዛል ተብሏል።
ከሰኔ 15-20 የሚካሄደዉ የህክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ሀገርአቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ ፖሊሲ አዉጪዎችና አስፈፃሚዎች ይሳተፉበታል።
በ-ሊያ ክብሮም












