፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 17 2016| NBC ETHIOPIA-የወቅቱ የአየር ንብረት መዛባት አለምን በእጅጉ ያስጨነቀና መፍትሔ ያልተገኘለት ጉዳይ ሆኗል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ በተጨማሪም ለተለያዩ ወረርሽኞች መከሰት ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡
የዘርፉ ችግር በአለም ኢኮኖሚው ፣ በህብረተሰብ ጤና ብሎም በማህበራዊ ህይወቱ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ባሻገር የመማር ማስተማር ስርዓቱን ማዛባት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በአለም ላይ ለትምህርት ከደረሱት ህጻናት ውስጥ 17 በመቶ ያህሉ ትምህርታቸውን በሙቀቱ ሳቢያ ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡
በዚህ ከልክ ያለፈ ሙቀት ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል መምህራንም ማስተማር ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ትምህርት ቤቶችን መዝጋት በተለያዩ ሀገራት የተለመደ ባህል እየሆነ የመጣ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሀገራት፣ ባንግላዲሸ፣ በፊሊፒንስ እንዲሁም ካምቦዲያ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
ትምህርት ቤቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ አድርጎ የማቆየቱ ልምምድ እንዳለ ሆኖ ተዘግተው የሚቆዩባቸው ቀናት ርዝመትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለ መምጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በ2021 በትምህርት ቤቶችና የሙቀት መጨመር ላይ በተደረገ ጥናት ከአስር አመት በፊት ከሶስት እስከ አራት ቀናት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በአሜሪካ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙቀት ምክንያት በየዓመቱ በአማካይ ከስድስት እስከ ሰባት ቀናት ከትምህርት ውጭ እንደሚሆኑ ጠቁሟል፡፡
የሙቀት ማዕበል በአንዳንድ ሀገራት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሲያስገድድ በሙቀቱ ምክንያት የመማር ማስተማር ስርዓትን ማከናወን ባለመቻል ትምህርት ቤቶችን ከዘጉ ሀገራት መካከል ህንድና ፓኪስታን ይገኙበታል፡፡
በህንድና ፓኪስታን ውስጥ የሙቀት መጠኑ ወደ 47 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴሊሸስ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ነው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የተወሰነው፡፡
የወቅቱ የአየር ንብረት በተማሪዎችና አስተማሪዎች ጤና እንዲሁም ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል ስጋት በመፈጠሩ ነው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የተወሰነው፡፡
በህንድና በፓኪስታን በርካታ አካባቢዎች ያሉ ባለስልጣናት በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት መገደዳቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

የህንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት በዋና ከተማዋ ኒው ዴልሂ የሚገኘው ናጃፍጋርህ አካባቢ ከፍተኛውን የሙቀት መጠን 47 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴሊሸስ ሲያስመዘግብ በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ከተሞች ደግሞ ከ45 ዲግሪ ሴሊሸስ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን እንዳስመዘገቡ ገልጿል፡፡
ባለስልጣናቱ በዋና ከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለክረምት ዕረፍት እንዲዘጉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሌሎች በርካታ የህንድ ግዛቶችም በጣም ሞቃታማ የአየር ጠባይ በማስተናገዳቸው ትምህርት ቤቶችን ወደ መዝጋት ሄደዋል፡፡
የሕንድ ሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት እንደገለጸው ይህ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚቀጥሉት በርካታ ቀናት ውስጥ እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል።
ብዙ ከተሞች በሚቀጥሉት ቀናት በ45 እስከ 46 ዲግሪ ሴሊሸስ የሙቀት መጠን ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በሙቀት መጨመር ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት በዝግጅት ላይ የምትገኘው ሀገር ፓኪስታን የሀገሪቱ መንግስት በፑንጃብ ግዛት የሚገኙ ሁሉንም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት ያህል እንደሚዘጋ አስታውቋል፡፡
በቀጣይ ሳምንት የተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ከግንቦት 25 እስከ 31 ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ይቆያሉ ሲል ይፋ አድርጓል።
ፓኪስታን በአሁኑ ጊዜ በ38ና 43 ዲግሪ ሴሊሸስ መካከል ባለው የሙቀት መጠን እየተናጠች ሲሆን ይህ የሙቀት መጠን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ 46 ዲግሪ ሴሊሸስ ከፍ እንደሚል ተገምቷል፡፡
ታዲያ ይህንን የወቅቱ የአለም ፈተና የሆነውን የሙቀት መጠን ለመቆጣጠር ያደጉ ሀገራት ይበጃል ያሉትን ሲያደርጉ ሰነባብተዋል፡፡
ለችግሩ አይነተኛ መፍትሔ ተብሎ የቀረበው ደግሞ ሙቀትን የሚቋቋሙ መማሪያ ክፍሎችን መገንባት ሲሆን 30 መሰል ትምህርት ቤቶችን እስከ 2026 ለመገንባት ማቀዱን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡
በየጊዜው እያየለ ለመጣው የአየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ መፍትሔ እንደሚያሻው በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡












