፨ ፨ ፨ ፨ ፨
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ ሰኔ 27 እና መስከረም 10 ላይ በአካል በመገናኝት የፊት ለፊት የምርጫ ክርክር ለማካሄድ የተቀጣጠሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት የቴሌቪዥን ፕሬዝዳንታዊ ክርክር ሰኔ 27 CNN በጆርጂያ ስዊንግ ግዛት ውስጥ ያስተናግዳል። ሁለተኛው የፊት ለፊት ክርክር ደግሞ በABC studio መስከረም 10 እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ይህ ማስታወቂያ የወጣው የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ፕሬዝዳንት ባይደን ከህዳር ምርጫ በፊት ከሪፐብሊካን እጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ፊት ለፊት ለመከራከር እንደሚፈልጉ ከተናገሩ በኋላ ነው። የሁለቱ ፖለቲከኞች የፊት ለፊት ክርክር ለተመልካች ዝግ ይሆናል የተባለ ሲሆን ባይደን በንግግራቸው መሀል ትራምፕ ጣልቃ ገብተው እንዳያቋርጧቸው ጥብቅ ትዕዛዝ ማዘጋጀታው አነጋጋሪ ሆኗል ፡፡ የባይደን የምርጫ አስተባበሪዎች ክረክሩ ያለ ተመልካች እንዲሆን ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል ፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ከተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመከራከር ዝግጁ ነኝ ሲሉ በኤክስ በድሮው ቲዊተር አካውንታቸው ላይ ጽፈዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ እባካችሁ ንገሩኝ መቼ ነው የምንከራከረው እኔ በየትኛውም ቦታ ፤ በተፈለገው ጊዜ፤ ወይም የትም ይመቸኛል ሲሉ መልሰዋል ፡፡
በዚህ ምርጫ በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፎካከራሉ፡፡ ሮበርት ኬነዲ ጁኒየር የግል ዕጩ ሆነው መቀርባቸው ቢታወቅም ሁለቱ ዋና ዋና እጩዎች እሳቸውን ለማግለል ተባብረዋል በሚል ክስ አቅርበው የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ለክርክሩ መስፈርቶችን እንደሚያሟሉ ለሲኤንኤን በ X በቀድሞ ትዊተር ገጻቸው አስፈርዋል፡፡

ሁለቱ የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ፓርቲ እጩዎች ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ቅድመ ግምት የተሰጠ ሲሆን እጩዎቹ በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው የእርስ በርስ ሽሙጦች ምርጫውን የበለጠ አጓጊ እንዲሆን አድርጎታል እየተባለ ይገኛል፡፡
ባይደን የትራምፕን የመድረክ ጉንተላ አብዝው እንደሚፈሩ አንዳንዶች ይገልጻሉ፤ ከዚህ በፊት ዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኛቸውን ባይደንን በታሪክ የከፋው መሪና ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን አንድ ላይ ማድረግ የማይችል በጣም መጥፎ ተከራካሪ ነው ሲሉ ወርፍ ማድረጋቸው ይታወሳል ።
ዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኛቸውን ጆ ባይደንን የፊት ለፊት ክርክር እናድርግ ሲሉ ከዚህ በፊት ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል ፡፡ትራምፕ የክርክሩን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እንደሚጠብቁት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የትራምፕ የምርጫ አስፈጻሚ ቡድን እንዳስታወቀው የአሜሪካ ህዝብ ከራሳቸው ከተወዳዳሪዎቹ የበለጠ ለመስማት ከሁለት በላይ እድሎች ሊኖሩት ይገባል፡፡
በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች በተደረጉ የቅድመ ምርጫ ጥናቶች ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሻለ ተቀባይነት እንዳገኙ ገልጸዋል ፡፡
የቀድሞ ነባር የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች እንደ ትራምፕ፣ ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽ እና ሮናልድ ሬጋን ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት በመጀመሪያው የጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ አስገራሚ ክርክሮች ያደርጉ እንደነበር ተንታኞች ይገልጻሉ።
የሰኔው ክርክር ከሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ ብሔራዊ ስብሰባዎች በፊት ይካሄዳል፡፡ የመስከረሙ ክርክር ደግሞ ከምርጫው ቀን ቢያንስ አንድ ወር በፊት ነው የሚከናወን ነው፡፡
ብዙ አሜሪካውያን እስከ መኸር ድረስ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዘመቻ ትኩረት መስጠት እንደማይጀመሩና ፕሬዚዳንታዊ ክርክሮች በተለምዶ በብዙ የአሜሪካ አውታረ መረቦች ላይ ከተሰራጩ በኋላ ህዝቡ መከታተል እንደሚጀምር ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት ። 73 ሚሊዮን አሜሪካውያን በ ትራምፕ እና ባይደን መካከል የመጀመሪያውን የ2020 ክርክር ተመልክተው እንደነበር ጥናቶች ያትታሉ::

የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በቀጣዩ ዓመት ህዳር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታደርግ ይታወቃል፡፡
በሁለቱ ጎምቱ ፖለቲከኞች የሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ክርክር ይበልጥ ተጠባቂ ሲሆን ከአሜሪካ ምርጫ ተሻግሮ የዓለማችንን የፖለቲካ መስመር መቀየስ የሚችል እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው ፡፡












