፨ ፨ ፨ ፨ ፨
ዓለማችን በልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሃብቶች የበለጸገች እና የታደለች ናት፡፡ ግዙፍ የበረዶ ግግሮች፣ አስደናቂ የመልካምድር አቀማመጥ፣ ጥቅጥቅ ደኖች፣ ፏፏቴዎች እንዲሁም ሌሎች እጅግ አስደናቂ ያልተነገረላቸው ተፈጥሮችን ታድላለች።
ለዛሬ በዓለማችን እጅግ ውብ የሆኑ እና የተፈጥሮን እጽብ ድንቅነት ያስመሰከሩ የተፈጥሮ መስህቦችን በጥቂቱ እናስመልክታችሁ።
????የአማዞን ጥቅጥቅ ጫካ

ሰፊው እና ጥቅጥቁ የአማዞን ደን ብራዚል፣ፔሩ እና ኮሎምቢያን ጨምሮ ደቡብ አሜሪካ ይሸፈናል። አማዞን በዓለማችን ላይ ትልቁ ጥቅጥቅ ደን ሲሆን፣ ከ40,000 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች 1,300 የወፍ ዝርያዎች ፣ከ 3,000 በላይ የዓሣ ዝርያዎች እንዲሁም ወደ 400 ቢሊዮን የሚጠጉ ዛፎች መገኛ ነው። ስፈራው እጅጉኑ ለአይን ማራኪ ከመሆኑ ባሻገር በውስጡ የሚገኙ ጠመዝማዛማ ወንዞች እና የከበቡት ድንቅ ተፈጥሮአዊ ስፍራዎች የጎብኚዎች ተመራጩ መዳረሻ አድርጎታል፡፡
ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ደን ስድስት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትርን እንደሚሸፍን የሚነገር ሲሆን፤ በምድር ላይ ከሚታወቁት ዝርያዎች 10 በመቶ ያህሉን መያዙ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
????የካፖዶሺያ መልከአ ምድር

በቱርክ በማዕከላዊ አናቶሊያ የሚገኘው ይህ ስፈራ በተለየ የመሬት አቀማመጡ በልዩነት ይታወቃል። አስደናቂ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ያለው ስፈራው ከ60 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በማዕከላዊ አናቶሊያ ከተከሰተው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በኃላ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡
በስፍራው መልከ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች እና ማራኪ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን፤ ከመላው ዓለም በርካታ ቱሪስቶች ይጎርፉበታል፡፡ የአየር ፊኛ ጉዞዎችም ቱሪስቶች ስፍራውን ከፍ ብለው ለመመልከት ተመራጩ ነው፡፡
ከአስደናቂ የመሬት ገጽታ በታች ተደብቀው የሚገኙ ‘ከመሬት በታች ያሉ ከተሞች’ ሌላኛው የቱሪስቶች መዳረሻ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በርካታ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ፤በቤተመቅደሶቹ መነኮሳት የተቀረጹ በርካታ ቅርሶች እና አስደናቂ የሆኑ ስዕላት ይገኛሉ።
እ.ኤ.አ በ2019 ብቻ 3.8 ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶች ወደዚህ ስፈራ አቅንተዋል።
????ዳንኪሲያ ላንድፎርም ፤ ቻይና

ዳንክሲያ ላንድፎርም በቻይና የሚገኝ የጂኦሎጂካል ፓርክ ሲሆን፤ በቀለማት ያሸበረቁ የተፈጥሮ ተራራ እና ቀይ የአሸዋ ድንጋይ የተከበበ ነው፡፡
የዳንክሲያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተለያየ መጠንና ቅርጽ ባላቸው በርካታ ዋሻዎች የተሞላ ሲሆን፤ መቶ ሜትር ከፍታ ያላቸው በርካታ ቀይ ቋጥኞችን አቅፎ ይዟል፡፡
ስፍራው በቀይ የአሸዋ ድንጋይ መሸርሸር ምክንያት እንደተፈጠረ ይነገራል፡፡ መልክዓ ምድራዊ አወቃቀሩ ፣ ከቀስተደመናማ የስፍራው መልክ ጋር ተዳምሮ ስፈራውን ልዩ አድርጎታል። በርካቶች ዳንኪሲያ ላንድፎርምን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡
????በጃፓን የሚገኙ የአራሺያማ የቀርከሃ ጫካዎች

ስፍራው ከጃፓኗ ኪዮቶ ወጣ ብሎ የሚገኝ ሲሆን፣ ረጃጅም የቀርከሀ ዛፎች እና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች ይገኝበታል።
አራሺያማ የቀርከሃ ጫካዎች፣ በአለም ላይ በብዛት ፎቶግራፍ ከተነሱ ቦታዎች አንዱ ስለመሆኑ ይነገራል። ይህንን አስደናቂ በቀርከሃ ዛፎች የተከበበ ስፍራ ለመመልከት በርካቶ በየዓመቱ ወደዚህ ስፈራ ያቀናሉ።
ይህ የቀርከሃ ጫካ በልዩነቱ የሚታወቀው የቀርከሃ ዝርያ የሚገኝበት ነው፡፡ ይህ የቀርከሃ ዝርያ እስከ 92 ጫማ ከፍታ ያለው እና እጅግ የሚያምር እይታን የተላበሰ ነው። የቀርከሃ ዛፉ የቦታው ተፈጥሯዊ ውበት በመሆኑ ተወዳጅ መዳረሻ እንዲሆን አስችሎታል። በጫካ ውስጥ እየተንጎራደዱ የእግር ጉዞ ለቱሪስቶች ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡
????በማሌዥያ ካሜሮን የሚገኙ አስገራሚ ተራሮች

በካሜሮን ከባህር ጠለል በላይ ከ2000 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ተራሮች የተፈጥሮን ውበት በሌላ መልክ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በማሌዥያ በፓሃንግ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ስፍራው፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የሻይ እርሻዎች ፣ የእንጆሪ እርሻዎች ፣ሸለቆዎች እንዲሁም ተራራማ ኮረብታዎች ይገኙበታል፡፡
አካባቢው ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ የተላበሰ ሲሆን፣ በፏፏቴዎች፣ በወንዞች፣ በሐይቆች፣ በዱር እንስሳት እና በልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሽልማቶች የደመቀ ነው፡፡ የስፈራው አስደሳች መልክዓ ምድር እና ቀዝቃዛ የአየር ጠባዩ ደግሞ የጎብኝዎች ተመራጭ ስፍራ አድርጎታል፡፡
በ-ሀይማኖት ወርቁ












