፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 08 2016| NBC ETHIOPIA- በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ህዝቦች የሚጠቀሙበት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ነው፡፡ ዓለምን በአንድ መዳፍ በእኩል ሰዓት ማገናኘት የቻለ መተግበሪያ ጭምር፡፡ ከ20 አመታት በፊት ብቅ ያለው ፌስቡክ የፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገጽሲታወስ ስሙ ተነጥሎ የማይነሳው የፈጠራ ባለቤቱ ማርክ ዙከርበርግን እ.ኤ.አ. በ 2004 በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ በነበረበት ወቅት ነበር የድረ-ገጹ ሶፍትዌርን ያዘጋጀው፡፡
ዙከርበርግ ከክፍል ጓደኞቹ ኤድዋርዶ ሳቬሪን፣ ደስቲን ሞስኮቪትስ፣አንድሪው ኮለም እና ክሪስ ሂዩዝ ጋር በመሆን ነበር ሶፍትዌሩን ማበልጸግ የቻሉት፡፡ በወቅቱ ዙከርበርግ እና ጓደኞቹ እያንዳንዳቸው 1,000 ዶላርን በመተግበሪያው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ይስማማሉ፡፡
ይሁንና ሶፍትዌሩን ወደ መተግበሪያ ለውጦ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ማስቻል እንዲ በቀላሉ የሚሆን ነገር አልነበረም፡፡ ፌስቡክ በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ነበረት፡፡ የተጠቃሚዎችን ትኩረትን መሳብ ደግሞ ትልቁ ፈተና ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት እንደ ማይስፔስ እና ፍሬንድ-ስተር ካሉ የማህበራዊ ድረ-ገጾች ከባድ ፉክክር ገጥሞት ነበር። ለኩባንያው የሚያስፈልጉ አጠቃላይ ወጪዎችን መሸፈን አለመቻል ደግሞ ሌላኛው ተግዳሮት ሆነ፡፡
ከሁሉም የከፋው ችግር ግን በመስራቾቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ነበር፡፡ በፌስቡክ ምስረታ ውስጥ ግማሾቹ ሀሳባቸውን በማዋጣት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ለመተግበሪያው ስራ ማስፈጸሚያ ገንዘባቸውን ፈሰስ በማድረጋቸው መተግበሪያው ለዓለም ህዝብ እንዲተዋወቅ ቢያደርጉም መተግበሪያው ተቀባይነት እያገኘ ሲመጣ ግን በተደጋጋሚ የፈጠራ ባለቤትነት ጥያቄን የመነጣጠቁ ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ከሰፊ ክርክሮች በኋላ ዙከርበርግ የመተግበሪያው ብቸኛ ባለቤት መሆን ቻለ፡፡ ይህም በጓደኛማቹ መካከል የነበረው ወዳጅነት እንዲበጠስ እና የከረረ ክስ ውስጥ የከተተ አለመግባባት ፈጥሮ ነበር፡፡

ፌስቡክ በጅማሮው የግለሰቦች እና የድርጅቶች መረጃ ደህንነትን ይጋፋል የሚል ሰፊ ትችት አስተናግዶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማህበራዊ ሚዲያው በአእምሮ ጤና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ያስፋፋል በሚልም ተግዳሮቶችን አስተናግዷል፡፡ እነዚህ እና መሰል ወቀሳዎች ሰዎች በፌስቡክ ላይ ያላቸው እምነት እንዲቀንሱ በማድረግ ሌሎች መተግበሪያዎችን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ ሲያደርግ ነበር፡፡ ሆኖም በዓለማችን ከፍተኛ የተጠቃሚዎች ቁጥር ያለው ፌስቡክ በየወሩ ከ3 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቋሚነት እስከ ማስተናገድ ደርሷል ይላሉ መረጃዎች፡፡ በምስረታው አመት ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ፌስቡክ እ.ኤ.አ በ2004 መጨረሻ አንድ ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ማፍራት ችሎ ነበር፡፡ ዩቲዩብ እና ኢንስታግራምን በማስከተል ፌስቡክ ቁጥር አንድ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ያሉት የዓለማችን የማህበራዊ ትስስር ገጽ መሆን ችሏል፡፡ ይህም 37 በመቶ የሚሆነው የአለም ህዝብ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ናቸው እንደማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2023 የተጣራ ትርፉ 39 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፤ ይህም በባለፈው ዓመት ካገኘው የ23.1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

በጅማሮ በርካታ ትችት እና ፈተናዎችን ያለፈው የዙከርበርግ ፌስቡክ፤ ዛሬም በርካታ ትችቶችና ወቀሳዎች ቢቀርቡበትም በእያንዳንዱ ስልክ ላይ የማይታጣ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መሆን ችሏል፡፡ በሜታ ኩባንያ ስር ከሆኑት ሜሴንጀር፣ ኢንስታግራም ትሬድስ የተሰኙት የማህበራዊ ትስስር ገጾች አንዱ የሆነው ፌስቡክ፣ በትርፍ መንገጫገጭ ጋር ተያይዞ የአክሲዮን ዋጋው እና ትርፉ ማሽቆልቆል ቢያሳይም በ2023 “የስኬት ዓመት” ማሳለፉን ይገልጻል፡፡
መልዕክቶችን በማጋራት የተጀመረው የፌስቡክ መተግበሪያ ጉዞ ምስሎችን እና ድምጾችን በማከል እንዲሁም ራሱን በልዩ ልዩ በማዘመን አለምን በቅርበት በማስተሳሰር የቅርብ የ20 አመታት ጉዞን ማድረግ ችሏል፡፡












