ሙስና ለበርካታ የአለማችን ሀገራት እድገት ፀር የሆነ ጉዳይ ነው በተለይ በአፍሪካ የሚገኙ ሀገራት ለእድገታቸው ማነቆ ሆኖ ይገኛል፡፡
በአፍሪካ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቀነስ አላማ አድርጎ በተካሄደው የፀረ-ሙስና ኤጀንሲዎች ጉባኤ ሙስና አሁንም የአህጉሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚው እድገት እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡
ከፈረንጆቹ ግንቦት 6 እስከ 11 ከ21 የአፍሪካ አባል ሀገራት የተውጣጡ የፀረ-ሙስና ኤጀንሲ ሃላፊዎች የተሳተፉበትና ቀጠናዊ የፀረ-ሙስና ጥረቶችን ለማጎልበት ያለመው ጉባኤ በጋና አክራ ተካሂዳል፡፡ ይህ ተቋም በአፍሪካ ስር የሰደደውን ሙስና ለመዋጋት አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦች በማቅረብ ሙስናን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በየአመቱ ይመክራል፡፡ በ14ኛው ጉባዔ “ተቋማትን ማጠናከር እና ግልጽነትን ማሳደግ ፤ ሙስናን በኮመንዌልዝ አፍሪካ የመዋጋት ዘዴ” በሚል መሪ ቃል የአፍሪካ የጸረ-ሙስና ኤጀንሲ የመሪዎች ጉባኤ ላለፉት ቀናት ተካሂዳል፡፡

ኮንፈረንሱ ሙስና በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ላይ የሚያደርሰውን አስከፊ ተጽእኖ ለመዋጋት አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ያለመ መሆኑም ተመላክታል፡፡
የአፍሪካ የፀረ-ሙስና ኤጀንሲ ማህበር አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የልማት አጋሮች በጉባኤ ተሳትፈዋል፡፡
በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማስቀጠል፣ እውቀትና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ፣ ሙስና በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ላይ ስለሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች በመወያየት እና ሙስናን በመዋጋት ረገድ አዳዲስ አሰራሮችን ለመፍጠር ያለመ ውይይት መከናወኑን የኮመንዌልዝ ሴክሬታሪያት የህዝብ ሴክተር አስተዳደር ኃላፊ ዶክተር ሮጀር ኮራንቴንግ ለአፍሪካ ኒውስ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ በየአመቱ ከሙስና ጋር በተያያዘ በርካታ ሚሊዮን ዶላር የምታጣ ሲሆን በሙስና የሚጠፋውን ገንዘብ ለመከላከል የፀረ ሙስና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ብሎም ግልፀኝነትን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአህጉሪቱን እድገት በተንሰራፋው ሙስና በእጅጉ እየጎዳ ነው ያሉት ዶክተር ሮጀር መሰረታዊ እንደ ጤና ፤ትምህርት ፤መብራት እና ውሃ ላይ ያለው ተፅእኖው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ሀገራት ሙስናን በመከላለከል ረገድ ሚሰሩት ስራ አነስተኛ መሆኑ ነገሩን አሳሳቢ አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ቦትስዋና ሩዋንዳ ሞሪሺየስ ያሉ ሀገራት ሙስናን በመከላከል ነገር ጥሩ ጅማሮን ማሳየት መጀመራቸው በመድረኩ ተገልፃል፡፡
ሲሺየልስ ሙስናን በመዋጋት ረገድ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን ዝቅተኛ ሙስና ወንጀል ከሚፈፀምባቸው ሀገራትም ቀዳሚ መሆናን ሃላፊው ተናግረው ለሌሎችም ምሳሌ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

በአፍካሪ በቂ የሰውና የፋይናንስ ሀብት በመኖሩ የፀረ ሙስና ኤጀንሲዎች ሙስናን በሚፈለገው ረገድ እንዳይከላከሉ ተግደሮት ሆኖባቸዋል ያሉ ሲሆን የህጎች ተግባራዊ አለመሆን ዋነኛው እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሙስና ወጪ በየዓመቱ ከ3.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በሙስና የሚመዘበረው የሚጠፋው ገንዘብ ለልማት ከዕርዳታ ከሚገኘው ገቢ 10 እጥፍ ይበልጣል፡፡
አፍሪካ በህገወጥ የገንዘብ ፍሰት በዓመት ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች። 21 የአፍሪካ ሀገራት የፀረ-ሙስና ኤጀንሲዎችን ያቀፈው በኮመንዌልዝ አፍሪካ ውስጥ የፀረ-ሙስና ኤጀንሲ ኃላፊዎች ማህበር እ.ኤ.አ በ2011 ከተመሠረተ ጀምሮ ኮንፈረንሱ በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡












