ጥበብ ለአንዳንዶች ዘግይታ የምትገለጥ፣ አድክማ የምትገኝ እረፍት ብትሆንም ለሌሎች ከተፈጥሮ ተሸልመዋት ስትመነዘር እንመለከታለን፡፡
አብዛኞቹ ህጻናት አፍ ለመፍታት በሚጥሩባት እድሜ፤ የ4 ዓመቱ ማክስ አሌክሳንደር ከእውቅ ዲዛይነሮች አዕምሮ ይፈልቃል ተብሎ የሚጠበቀው የፈጠራ ባለቤት ሆኗል፡፡
በደቡብ ካሊፎርኒያ የሚኖረው እና በእድሜ ትንሹ ዲዛይነር ማክስ ከልጅነቱ ጀምሮ ልብሶችን እየነደፈ እና በተለያየ ዲዛይኖች እየሰራ ይገኛል፡፡ ባለፈው ህይወቴ ተፅዕኖ ፈጣሪው ዲዛይነር እና የውድ እና ቅንጡ ልብሶች አቅራቢ ጉቺ ካምፓኒ መስራች (ጉቺ ጉቺ) Guccio Gucciን ነበርኩ ሲል ይቀልዳል፡፡
የ7 አመቱ ማክስ አሌክሳንደር ገና በ 4 አመቱ የተዋበ የተባለ ቀሚስ በመስራት ጉድ አስብሏል፡፡ እለት ተእለት ስራውን በአለም አቀፍ ደረጃ በመሸጥ እና ከታዋቂ ሰዎች ኮሚሽን በመቀበል የልጅ ሀብታም ሆኗል፡፡
ማክስ ከእናቱ ሼሪ ማዲሰን ጋር በመሆን በልብስ ዲዛይን ስራው ግሩም ያስባሉ ቀሚሶችንና ሌሎች ልብሶችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም የማክስ ልብሶች በዓለም ዙርያ ገበያውን እንዲቆጣጠሩት እያደረገ ነው፡፡
የዚህ ባለጥበብ እናት ማዲሰን ስለልጇ ስትናገር፡- የማክስን የዲዛይን ክህሎት መጀመሪያ ላይ እንዳላወቀች እና በ 4 አመቱ ግን የተለያዩ አይነት ልብሶችን የመስራት ክህሎት እንዳለው እንደተረዳች ትናገራለች፡፡

በጣም ነው ድንቅ የሚለኝ አንዳንዴ እንደውም እሱ ነው ሚሰራቸው ብዬ ተደብቄ አይቼም አውቃለው ትላላች እናቱ፡፡ ምንም ትምህርት እና ልምምድ በሌለበት ገና በ4 ዓመቱ የሰራውን ቀሚስ ስመለከት ደንግጫለው ትላለች፡፡
ባለ ንቁ አዕምሮው ማክስ አያቶቹ የልብስ ስፌት ባለሙያዎች እንደነበሩ የሚናገሩት ቤተሰቦቹ ምናልባት በዘር የወረሰው ተሰጥኦ ይሆናል ይላሉ፡፡
የሌሎች የሁለት ልጆች እናት የሆነችው እናቱ ማዲሰን፣ ልጄ በርካታ ልብሶችን ከሰፋ በኋላ ስፌት መማር እንደሚፈልግ መወትወት ጀመረ ፡፡
ያው ትንሽ መሰሰት አለ አይደል ገና 4 ዓመቱ ነው … ብቻ ትንሽ ካሰብኩበት በኋላ እንዴት በማሽን መስፋት እንደሚቻል አሳየሁት፤ ሁለት ሳምንት አልፈጀበትም እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ደንበኛ ሰፊ መስፋት ጀመረ፡፡ ከዚያም በሰፈራችን አሉ ወደተባሉ ስፌት ቤቶች እወስደው ጀመር እዛም ክህሎቱን ማሳደግ ገባ በቃ ዛሬ እዚህ የደረሰበት ላይ ይገኛል፡፡ ትላለች

‹‹በጣም ቁርጠኛ ነው ስህተቶች ሲሰራ እራሱ በቀልድ እያለፈ እራሱን እያረመ እንደልጅም እንደ አዋቂም የሆነ ልጅ ነው፡፡ አብዝቶ የሚሰራቸው የሴት ልብሶች ናቸው ሴቶች ሁሌም ውበት ሊሰማቸው ይገባል ይላል በእውነቱ ስመለከተው በጣም ደስ ይለኛል›› ትላለች ማዲሰን
በጥቂት አመታት ውስጥ ማክስ ከመቶ በላይ ዲዛይኖችን ሰርቷል፣ ስራውን በአለም አቀፍ ደረጃ እየሸጠ ነው፡፡ የራሱን የፋሽን ትርኢቶች የሚያቀርብበት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ ለአሜሪካዊቷ እውቅ ተዋናይት እና ሰዓሊ ሻሮን ስቶን ጃኬት ሰርቶ አልብሷል።
ማክስ ትልቅ ህልም አለው፡፡ ወደ ዲዛይን መግባት ለሚፈልጉ ልጆች በር የከፈተ ነው፡፡ “ልምምድ ፍጹም ያደርገዋል” የሚለውንም ከክህሎቶ መዳበር መገንዘብ ይቻላል፡፡

ወርቃማ ልብ አለው የምትለው እናቱ፣ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ሰዎችን ለማስደሰት በማሰብ ነው.፤ በእነዚህ ልብሶች ላይ ያለው አላማም ሰዎች ውበት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው ይህንን ነው ሁሌ የሚነግረኝ ትላለች፡፡
ወደፊት መቀመጫውን ፓሪስ ያረገው እውቁ የውድ እና ቅንጡ ልብሶችና ጌጣጌጦች አቅራቢ ኩባንያ Gucci ኃላፊ መሆን ይፈልጋል ጥበብ በሰጠችው ስጦታ በፋሽን ኢንደስትሪው በጣም ተፅዕኖ መፍጠር ህልሙ ነው፡፡












