ከዓለማችን የተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አይነት ጉድ ያስባሉ የሰርግ ስነ-ስርዓቶችን እና ድግሶችን እንመለከታለን፡፡ ለዛሬ በዓለማችን ካሉ ያልተለመዱ የሰርግ ስነ-ስርዓቶች የተወሰኑትን እንንገራችሁ፡፡
የሙሽሪት የለቅሶ ልምምድ
ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ የሚለው የሀገራችን ብሂል በሙሽርነት ጊዜ የእንባ ዘለላዎችን ማፍሰስ የተለመደ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከወደ ቻይና የተሰማው ግን ከዚህ የተጋነነ ሆኗል፡፡
በቻይና የቱጂያ ማህበረሰብ ሙሽሪት፤ ከሰርጓ በፊትና በሰርጓ ቀን ማልቀስ ግድ ይላታል፡፡የቱጂያ ሴት ልጆች ገና ከ12 እድሜያቸው አንስቶ ወደፊት ለትዳራቸው እንዴት ጥሩ አልቃሽ መሆን እንዳለባቸው ይማራሉ፡፡

ሙሽሪት ከሰርጓ ቀን አንድ ወር በፊት ሰፋ ያለ ዜማ ያዘለ የለቅሶ ልምምድ ማድረግ የሚጠበቅባት ሲሆን፣ በእያንዳንዱ የልምምዱ ቀናት በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ያህል እንባዋን ታፈሳለች፡፡ ከአሥር ቀናት በኋላ እናት ለቅሶውን የምትቀላቀል ሲሆን፤ የሙሽሪት አያትም እንዲሁ ሙሽሪትን ለማላቀስ እና ለቅሶዋን ለመገምገም ትቀላቀላለች፡፡
በምዕራብ ሲቹዋን ግዛት ዙኦ ታንግ እንደተጀመረ የሚነገረው ልምዱ፤ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በቻይና የጦርነት ግዛቶች ዘመን ዛኦ የተባለች ልዕልት በሠርጓ ቀን ከእናቷ ጋር ያነባችውን እንባ በማሰብ እንደሚከወን ይነገራል፡፡
ይህ ስነ-ስርዓት በቱጂያ ማህበረሰቦች በስፋት የተለመደ ቢሆንም በሌሎች የቻይና አካባቢዎችም ይካሄዳል፡፡
የሙሽራውን እግር መጠብጠብ

በደቡብ ኮሪያ አንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ ወንድ ሙሽራ ከሰርጉ በፊት ውስጥ እግሩን በጣውላ መደብደብ ግድ ይለዋል፡፡
ሙሽራው እግሩ ሳይመታ ሙሽሪትን ወደቤቱ መውሰድ አይችልም፡፡ የቤተሰብ አባላት የሙሽራውን ውስጥ እግር ላይ ዱላ ለማሳረፍ ወረፋ ከያዙ በኋላ ቁርጭምጭሚቱን በገመድ አስረው እግሮቹን በዱላ አልያም በደረቀ አሳ ይቀጠቅጣሉ፡፡
ጥብጠባው ረጅም ጊዜ የማይወስድ ቢሆንም ግርምት ዱላ አሰናዘሩ እጅ በአፍ ያስጭናል፡፡ ስርዓቱ በአካባቢው ማህበረሰቦች ዘንድ የሙሽራውን ባህሪ ቀድሞ ለመፈተሸ እና ለቀጣይ ትዳሩ ጠንካራ አባወራ እንዲሆን ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡
የማሌዥያ ሙሽሮች አስገራሚ ጉዳይ

በማሌዥያ ሙሽሪት እና ሙሽሪት መታጠቢያ ቤት መጠቀም አይፈቀድላቸውም፡፡
በማሌዢያ እና በኢንዶኔዢያ ቲዶንግ ቦርንዮ የማህበረሰብ ክፍሎች ሙሽራ እና ሙሽሪት ከሠርጋቸው ስነ-ስርዓት በኋላ ለሦስት ቀናት ጠባቂ ተዘጋጅቶላቸው ቤታቸውን ለቀው እንዳይወጡ እና አነስ ያለ ምግብና መጠጥ እየተሰጣቸው መጸዳጃ ቤት እንዳይጠቀሙ ይከለከላሉ፡፡
ይህንን ያላደረጉ የሙሽሮቹ ቤተሰቦችም ሆኑ ወዳጅ ዘመዶች የሙሽሮቹን ቀጣይ እጣ ፈንታ እንዳበላሹ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም ስርዓቱን ሙሽሮቹም ሆነ ወዳጆቻቸው አይቃወሙትም፡፡
ወደ አፍሪካ ስንመጣ በኬንያ እና በታንዛኒያ የማሳኢ ጎሳዎች፣ የሰርግ ስነ-ስርአት ያልተለመደ ነው፡፡

በማሳኢ ባህላዊ የጋብቻ ስነስርዓት ላይ የሙሽሪት አባት ሙሽራዋ ጭንቅላት ተላጭቶ የበግ ስብና ዘይት ከተቀባች በኋላ፤ የሙሽራዋ አባት ሴት ልጁን ጭንቅላቷ እና ቀሚሷ ላይ በመትፋት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ይህም የፍቅሩ እና የመልካም ምኞቱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በባህል እንደ ንቀት እና አስጸያፊ ተደርጎ የሚወሰደው ሰው ላይ መትፋት በማሳኢዎች ዘንድ የፍቅር ማሳያ ነው፡፡
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












