፨ ፨ ፨ ፨ ፨
የአለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ የገቢ መጠን ከአመት አመት ብልጫ እያሳየ መጥቷል፡፡በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ የሚገኘው አመታዊ ገቢ በድምሩ ወደ 1 ነጥብ 9 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።
በበርካታ ጎብኚዎች ከሚጎበኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መካከል ደግሞ ሀይማኖታዊ ቦታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡በርካታ ሀይማኖታዊ ተግባራት የሚከናወንባቸው ስፍራዎች ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል ቤተ ልሔም አንደኛዋ ናት፡፡
ቤተልሔም በዌስት ባንክ ከእየሩሳሌም በስተደቡብ 8 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ስፍራም ናት፡፡

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የሚሰጣት ቤተልሄም፣ በቁጥር የላቀው የእምነቱ ተከታይ ወደ ስፍራው ያቀናል፡፡
ሀይማኖታዊ መዳረሻ እንደመሆኑ በበዓላት ወቅት የጎብኚው ቁጥር ከወትሮው በርከት ይላል፡፡በተለይም በገና እንዲሁም ትንሳኤ በዓላት ወቅት የጎብኚዎች ቁጥር በብዙ ቁጥር ይጨምራል፡፡
እስራኤልና ፍልስጤም የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት በተለያዩ ጊዜያት ግጭት ውስጥ የሚገቡባት የቤተልሔም ከተማ የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ይገኙባታል፡፡ከተማዋ በርካታ ታሪካዊ ብሎም ሀይማኖታዊ መዳረሻዎች በውስጧ ሰብስባ ይዛለች፡፡
ቤተልሔምና ዙሪያዋ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ ትምህርት ቤቶች ብሎም ሆስፒታሎች ይገኛሉ።የመጀመርያው የክርስቲያን የሮማ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ 1ኛ ወላጅ እናት ቅድስት ሄለና በዋሻው ላይ ቤተ ክርስቲያን አሠራች።
በዚህም የኢየሱስ ልደት ቤተ ክርስቲያን በጥንት ከነበሩት አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ለመሆን ቻለ፡፡ቤተክርስቲያኑ በኋላ ላይ ጉዳት ቢደርስበትም በንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን አሁን ባለው መልኩ እንደገና ተሰርቷል።እነዚህን ጨምሮ በርካታ የዘመናት ታሪክ ያላቸውን ሀይማኖታዊ ክንውኖች ለመታደም በየአመቱ ከሁለት ሚሊየን በላይ ጎብኚዎች ወደ ስፍራው ይጎርፋሉ፡፡

የቱሪዝሙ ዘርፍ እስከ 65 በመቶ የከተማዋን ኢኮኖሚና 11 በመቶ የሀገሪቱን እንደሚሸፍን ይነገራል፡፡ከቤተልሔም በአንድ መቶ ሀምሳ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው እየሩሳሌም የጎብኚዎችን ትኩረት የሳበው ሌላኛው ሀይማኖታዊ ስፍራ ጎለጎታ ይገኝበታል፡፡
ጎለጎታ በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ መጠሪያ ሲሆን ከእየሩሳሌም ወጣ ብሎ የሚገኝ ስፍራ ነው፡፡ይህም ሌላኛው የጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን እያገለገለ የሚገኝ ሀይማኖታዊ መስህብ ነው፡፡
ብዙ ወደ ሀገረ እስራኤል የሚጓዙ ጎብኚዎች እንደ ጎለጎታ ያሉ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቦታዎች መኖራቸው የጎብኚውን ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል፡፡በፈረንጆቹ 2017 እየሩሳሌም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቱሪስቶች የጎበኟት ከተማ ነች፡፡በዓለም ላይ ካሉት ጥንታዊ ከተሞች አንዷ የሆነችው እየሩሳሌም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦን ማድረግ ችላለች፡፡
በዚህም የሀገሪቱ ከዘርፉ ያላት ተጠቃሚነት በ2023 5 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ይህም በ2022 ከነበረው የ5 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ከፍ ጭማሪን አሳይቷል፡፡












