፨ ፨ ፨ ፨ ፨
ዓለም ላይ በየጊዜው በርካታ ሀይማኖታዊ መልዕክትን ያዘሉ ፊልሞች እና ተከታታይ ድራማዎች ይሰራሉ።እነዚህ ፊልሞች በሀይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅ ሲሆኑ ስለ ሀይማኖቱም ቢሆን ጥሩ ማስተማሪያ ናቸው። ሀይማኖታዊ ይዘቶችን በማስመልከት ጥልቅ የሆነ ትምህርት እና መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ነገ እሁድ በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የትንሳኤ በአል ምክንያት በማድረግ በዓለማችን ላይ የተሰሩ የኢየሱስ ክርስቶስን ከልደቱ እስከ ትንሳኤው ያለውን የህይወት ታሪክ የሚያስመለክቱ ፊልሞችን በጥቂቱ እናስቃኛችሁ።
1, From the Manger to the Cross በቅድሚያ የምናገኘው በ ጂን ጋውንቲ ተጽፎ በሲድኒ ኦልኮት ዳይሬክት የተደረገው From the Manger to the Cross የተሰኘውን ፊልም ነው። እ.ኤ.አ በ1912 የተለቀቀው ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም ድምፅ አልባ ፊልም ሲሆን በካለም ኩባንያ ተዘጋጅቷል።

ፊልሙም የተቀረፀው በግብፅ እና በፍልስጤም ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በማሰናሰን ይተርካል። በትወና አሜሪካዊው ሮበርት ሄንደርሰን ተሳትፎበታል።
ፊልሙ በአጠቃላይ የ70 ደቂቃ ርዝማኔ ሲኖረው የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት፣ የደቀ መዛሙርት ጥሪን፣ የተራራው ስብከትን፣ የዓይነ ስውራን ፈወስ፣ የአልዓዛርን ትንሣኤ፣ የመጨረሻው እራትን፣ ስቅለት እና ትንሣኤን ያሉ ትዕይንቶችን ያስመለክተናል፡፡ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ፊልም በቀጣይ ለተሰሩ ሀይማኖታዊ ፊልሞች ትልቅ ምዕራፍ ከፋች ነበር፡፡
ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ፊልም እ.ኤ.አ በ1952 የተሰራ ነው፡፡ The Life of Christ ይሰኛል፡፡ በአይርቪንግ ፒሼል ዳይሬክት የተደረገ ፊልም ነው። አዲስ ኪዳን ላይ ተመሰርቶ የተሰራው ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት የሚያሳይ ፊልም በብዙ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡

ፊልሙ የኢየሱስ ክርስቶስ ውልደቱን ፣ በልጅነቱ እና በመጨረሻ በአዋቂነት አገልግሎቱን ይተርካል። የተራራውን ስብከት ፣ የመጨረሻውን እራት ጨምሮ ተአምራቶቹን፣ ምሳሌዎችን እና ትምህርቶቹን ይዳስሳል።
ፊልሙ ፋሚሊ ቲያትር ፕሮዳክሽንስ በተሰኘ የካቶሊክ ፊልም ሰሪ ድርጅት የተሰራ ነው፡፡ ጄፍሪ ሀንተር የኢየሱስ ክርስቶስን መስሎ ተጫውቷል።
“የናዝሬቱ ኢየሱስ” የተሰኘው ፊልም እ.ኤ.አ በ1977 የተሰራ የሲሆን ለእይታ የበቃው በፍራንኮ ዘፊሬሊ ዳይሬክት ተደርጎ በአንቶኒ በርጌስ እና በሱሶ ሴቺ ዲ አሚኮ ተፃፏል። ይህ ፊልምም የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ከቤተልሔም ልደቱ እስከ ስቅለቱና ትንሣኤው ድረስ ይተርካል።
“የናዝሬቱ ኢየሱስ” በተመልካቾች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እና ከስድስት ሰአታት በላይ የሚዘልቅ ፊልም ነው።

ፊልሙ እምነትን፣ ርህራሄን፣ ቸርነትን እና በኢየሱስ እና በዘመኑ በነበሩት መሪዎች መካከል የነበረውን ግጭት ጨምሮ የተራራውን ስብከት፣ የመጨረሻው እራት እና ስቅለቱን ያሳያል።
The Jesus Film የተለቀቀው እ.ኤ.አ በ1979 ነው። ይህ ፊልም ከመጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ ወንጌል ላይ የተመሠረተ ነው። ፊልሙ የተሰራው በካምፓስ ክሩሴድ ፎር ክርስቶስ እና በፒተር ሳይክስ ሲሆን በጆን ሄይማን ዳይሬክት ተደርጓል።

ፊልሙ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት፣ ሕይወት፣ ትምህርት፣ ሞት እና ትንሣኤ ያሳያል። ፊልሙ የኢየሱስ ክርስቶስን ምድራዊ ቆይታ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምዕራፎች በማጣቀስ ለብዙ ተመልካቾች መድረስ ችሏል፡፡
ፊልሙ የተቀረፀው እስራኤል ሲሆን ፊልሙም የተሰራው በኢየሱስ ዘመን ይነገር በነበረው የአረማይክ ቋንቋ ነው።
5, The Passion Of The Christ
በዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ፥ ደራሲና ዳይሬክተር ሜል ጊብሰን ተፅፎ የተዘጋጀና ፕሮዲዩስ የተደረገ ፊልም ነው። ፊልሙ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻዎቹ አስራ ሁለት የስቃይና የስቅላት ሰዓታት ላይ አተኩሮ ተሰርቷል።

የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወት መሰረት አድርገው ከተሰሩት ቀደምት የሆሊውድ ፊልሞች በተለየ ሁኔታ The Passion Of The Christ የክርስቶስን እውነተኛ ስቃይ በተሻለ ሁኔታ አቅርቦ ስለመሰራቱ ብዙዎች መስክረውለታል፡፡
የፊልሙ ቋንቋንም በወቅቱ የነበረውን፥ ጥንታዊውን “አርማይክ” ቋንቋን ተጠቅሟል።ፊልሙም አጠቃላይም 30 ሚልዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።
በ-ሀይማኖት ወርቁ












