፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 24 2016| NBC ETHIOPIA- የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ባለስልጣናት በአመት መቶ ሚሊዮን ገደማ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው አል ማክቱም አለም ኣቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወይም ዱባይ ወርልድ ሴንትራል ለማልማት ማቀዳቸው ተገልፃል፡፡
የዱባይ ገዥ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ከዱባይ 28 ማይል ርቀት ላይ በሚገኘው አል ማክቱም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በ35 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የመንገደኛ ተርሚናል ለመገንባት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ የመንገደኛ ተርሚናሉን ለመገንባት ዲዛይን መፅደቁን ብሎም ግንባታ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
በማስፋፋያ ግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያው፤ ሲጠናቀቅ በምድራችን ካሉት አውሮፕላን ማረፊያዎች ሁሉ የላቀ እንደሚሆን የዱባዩ ገዢ ተናግረዋል፡፡አዳዲስ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በዚሁ አውሮፕላን ማረፊ ተግባራዊ ይሆናሉም ብለዋል፡፡
አል ማክቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስራውን የጀመረው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን፤የአሁኑ የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ በሀገሪቱ የተጨናነቀውን የበረራ አገልግሎት ለማሻሻል እንዲሁም ግንባር ቀደም አየር ማረፊያ ለማድረግ እንደሚረዳው የዱባይ ኤርፖርት ዋና ስራ አስፈፃሚ ፖል ግሪፍስ ከ CNN ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል፡፡

በመሃል ከተማ የሚገኘውና የሀገሪቱ ግዙፉ አየር ማረፊያ የሆነው ዱባይ አለም አቀፍ ኤርፖርት በሁለት ዋና ዋና መንዶች መሃል ላይ በመገኘቱ እና ለማስፋፊያ ስራ አመቺ ባለመሆኑ የአል ማክቱም አየር ማረፈያ ማስፋፊያ ማስፈለጉ ተመላክቷል፡፡
አዲስ የሚገነባው አል ማክቱም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወይም ‹‹ዱባይ ወርልድ ሴንትራል›› የመንደኞች ተርሚናል በ70 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ይገኛል፡፡
ተርሚናሉ አሁን ካለው ዱባይ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ እና በዓመት እስከ 260 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል፡፡ ኤርፖርቱ በዓመት ከ12 ሚሊዮን እሰከ 13 ሚሊዮን ቶን ጭነት ማመላለስ እንዲችል ተደርጎ ይገነባል ሲሉ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡
የተረሚናል ግንባታው ሲጠናቀቅ አምስት ትይዩ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ወይም ማኮብኮቢያዎች እና 400 የአውሮፕላን መግቢያ በሮች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
በአለም አቀፍ ጉዞዎች በጣም የተጨናነቀው የዱባይ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚቀጥሉት አመታት ስራውን ወደ አዲሱ አል ማክቱም አለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደሚዘዋወርም ይጠበቃል፡፡
የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሀመድ ቢን ራሺድ ፣የተረጋጋ እድገትን ለቀጣይ ትውልድ ለማረጋገጥ አዳዲስ ፕሮጅክቶችን እየገነባን ነው ያሉ ሲሆን ዱባይ የዓለም አውሮፕላን ማረፊያ እና አዲስ ዓለም አቀፍ ማዕከል ትሆናለች ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የዱባይ ኤርፖርቶች ዋና ስራ አስፈፃሚ ፖል ግሪፍስ በበኩላቸው እድገቱ የዱባይን መሪ የአቪዬሽን ማዕከልነት ደረጃን ያጠናክራል ብለዋል ።
የዱባይ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለ10 ተከታታይ አመታት በአለም አቀፍ ጉዞ በጣም የተጨናነቀ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኖ የተቋሙን አቅም ጫና ውስጥ መጣሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 87 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን ማስተናገድ ችሏል፡፡ ዱባይ እ.ኤ.አ. በ2023 17.15 ሚሊዮን አለምአቀፍ ጎብኝዎችን እንዳስመዘገበች የተገለፀች ሲሆን ይህም ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር ወደ 20 በመቶ ገደማ ጨምሯል።
የዱባይ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ፕሬዝዳንት እና የኤሚሬትስ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሼክ አህመድ ቢን ሰኢድ አል ማክቱም የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።
በአል ማክቱም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንደተጠናቀቀ የወደፊት አዲስ የመንገደኞች ተርሚናል ግንባታ እንደሚጀመርም ተጠቁሟል፡፡












