፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 24 2016| NBC ETHIOPIA- የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ለመጪው የትንሳኤ በዓል ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት አድርጊያለሁ አለ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መጪውን የትንሳዔ በዓል በተመለከተ ስላደረጉት ዝግጅት አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ላለፈው አንድ ወር ኮሚቴና ግብረሃይል በማቋቋም የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የገለፀው ፅህፈት ቤቱ በፅዳት፣ በኤሌክትሪክ ሃይልና የውሃ አቅርቦት ብሎም ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በበዓላት ወቅት የሚከሰቱ አብዛኞቹ አደጋዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ የሚከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን የከተማዋ እሳትና ድንገተኛ አደጋ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ ህብረተሰቡ በበዓላት ወቅት የሚመረትን ቆሻሻ በአግባቡ እንዲያስወግድ ጠይቋል፡፡ በበዓሉ ቀን የሀይል መቆራረጥ እንዳይኖር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ያስታወቀው ደግሞ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው፡፡ ደንበኞቹ በበዓላት ቀን አገልግሎት ወደሚሰጡ ማዕከላቱ በመሄድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር ጥንቃቄ እንዳይለየው ያሳሰቡት ተቋማቱ ለመጪው የትንሳኤ በዓል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በ-መቅደስ ደምስ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












