፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 18 2016| NBC ETHIOPIA-ግዙፉ የአሜሪካው ሜታ ኩባንያ ካቀደው በላይ ገቢ ቢያስመዘግብም አክስዮኖቹ መመናመን አጋጥመውታል ተባለ፡፡ የፌስቡክና ኢንስታግራም ባለቤቱ ሜታ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ላይ ከፍተኛ ወጪ ፈሰስ እያደረገ በመሆኑ የእዚህ አመት ወጪው እንደሚጨምር ገልጿል፡፡
ቀደም ካሉት ጊዜያት በበለጠ በ2024 በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ እንደሚደርግ መተንበዩን ተከትሎ የአክሲዮን ድርሻው ከ15 በመቶ በላይ ማሽቆልቆሉ ነው የተሰማው፡፡
ሜታ ገቢውን ለማሳደግ የሰው ሰራሽ አስተውህሎትን በመጠቀም የሽያጭ ማስታወቂያዎቹ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡ እገዛ የሚሹ ደንበኞቹን በማገዝና ጥያቄዎችን በብቃት በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ እንደሚያግዘው ቻት አሲስታንት ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤቶችንም የማህበራዊ ትስስር መተግበሪዎቹ ላይ እያዋለ ነው፡፡
መሰል ለውጦችን ለማድረግ በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 ከ35 እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊያደርግ ማቀዱን እወቁልኝ ብሏል፡፡ ቀደም ሲል አስቀምጦት የነበረው ግምት ከ30 እስከ 37 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ የአክሲዮኖቹ ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ኩባንያው በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 36.16 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያገኝ ተንታኞች ካስቀመጡለት ትንበያ በልጦ 36.46 ቢሊዮን ዶላር ወደካዝናው አስገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው የያዛቸው ከፍተኛ የወጪ እቅዶች የተጋነኑ ናቸው በሚል በብዙዎች እያስተቸው ይገኛል፡፡
ቲክቶክን ከአሜሪካ ምድር የማገድ አልያም ድርሻውን የመሸጥ እንቅስቃሴ ሜታን አትራፊ እንደሚያደርገው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡ የሜታ ተቀናቃኝ ቲክቶክ በበኩሉ የተጀመረውን ኢ-ህገመንግስታዊ ያለውን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚቃወምና እንደሚታገለው ጭምር እየገለጸ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ባይደን ለማህበራዊ ሚዲያው ቲክቶክ ኩባንያ የዘጠኝ ወራት የጊዜ ገደብ የሚሰጠውን ህግ ፈርመዋል፡፡
ቴክቶክ ያለበት ሁኔታ ለሜታ ተጨማሪ መልካም እድሎችን የሚፈጥር ስለመሆኑ የምትገልጸው ሶፊ ሉንድ ዬትስ ይህ ማለት ግን የድርጅቱን ቀጣይ ጉዞ አልጋ በአልጋ የሚያደርግ አይደለም ትላለች፡፡

ባለፈው አመት ሜታ ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ የተላኩ የደንበኞቹን መረጃዎች በአግባቡ አልያዘም በሚል በአየርላንድ የመረጃ ባለስልጣናት የ1.2 ቢሊዮን ዩሮ ቅጣት ተቀጥቷል፡፡
ከወሲባዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘው ልጆችን ለወሲባዊ ብዝበዛ ዳርጓል በሚልም በተያዘው ዓመት የካቲት ላይ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ ሰለባ ናቸው የተባሉትን ታዳጊዎች ቤተሰቦች ይቅርታ እንዲጠይቅ ከአሜሪካ ህግ አውጪዎች ከባድ ትችትና ግፊት ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሜታ በርካታ ገንዘብ የሚያስወጡ ክሶችና ወቀሳዎች በበረቱበት ወቅት በተያዘው ዓመት ወጪዬ ይሆናል ያለው ከ35 እስከ 40 ቢሊዮን የሚደርስ ወጪ በእንቅርት ላይ እንዲሉ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍለው እየተነገረ ነው፡፡
ድርጅቱ ችሎት ለሚያስቆሙት ክሶች የሚሆን የገንዘብ ችግር ባይኖርበትም ገበያው ላይ እንቅፋት ከመፍጠር አያተርፈውም በሚል በርካቶች እያስጠነቀቁ ነው፡፡












