፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 08 2016| NBC ETHIOPIA-እስራኤል ከሁለት ሳምንታት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ፅህፈት ቤት ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወሳል፡፡ ኢራን በደማስቆ ለደረሰው ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ወደ እስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች፡፡ ይህንንም ተከትሎ በእስያ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱ ተሰምቷል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ተመንን የሚዘውረው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል 90 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ አሻቅቦ የነበረ ሲሆን ኢራን በእስራኤል ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ ዋጋው በ 1በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሚል 92.18 ዶላር የነበረ ሲሆን ከጥቅምት ወር ወዲህ ዋጋው ከፍተኛ ነበር፡፡ ተንታኞች እስራኤል ለጥቃቱ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ በአለም ገበያ ወሳኝ የንግድ ለውጦችን ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ሀገሪቷ በእስራኤል ላይ ያደረሰችው ጥቃት ተፅእኖው በዓለም ዓቀፍ የነዳጅ ዋጋ ብቻ ሳይሆን በእስያ-ፓሲፊክ ቀጠና የአክሲዮኖች ሽያጭ ዋጋ ገና ከአሁኑ ማሽልቆል ጀምሯል፡፡ በሆንግ ኮንግ የሚገኘው ሃንግ ሴንግ፣ የጃፓኑ Nikkei 225 እና በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ኮስፒ ሲያካሄዱት የነበረው የአክሲዮን ሽያጭ መጠን መቀነሱን ቢቢሲ በቢዝነድ አምዱ አትቷል፡፡

ሌላኛው የዋጋ ጭማሪ ያሳየው ወርቅ ነው፡፡ 31.1 ግራም የሚመዝነው አንድ አውንስ ወደ 2,400 ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ጨምሯል፡፡ የወርቅ ንግድ አስተማማኝ ኢንቬስትመንት አይነቶች ከሚባሉት መሃከል ሲሆን በሚያስደንቅ ሁኔታ የዋጋ ለውጥ ሊያሳይ ችሏል፡፡ በኦማን እና በኢራን መካከል ያለው የባህር ዳርቻ በሆርሙዝ ሰርጥ ዋነኛው የባህር ትራንስፖርት የሚካሄድበት መንገድ ሲሆን ከዓለም አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት 20% ያህሉ የሚጓዝበት መስመር ነው፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች በፐርሺያ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ መካከል በሚገኘው የሆርሙዝ የባህር ዳርቻን፤ በአማራጭነት መጠቀም በንግድ መስመሩ እንዲሁም በቀጣይነት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የኦፔክ አባል ሀገራት ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኩዌት እና ኢራቅ የሆርሙዝ የባህር ዳርቻን በመጠቀም ነዳጅ ወደ ሌሎች ሀገራት ይልካሉ፡፡
ኢራን ከዓለም ሰባተኛዋ እንዲሁም ከኦፔክ አባል ሀገራት 3ተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ አምራች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በ2023 የኢራን ስታቲስቲክ ማእከል መረጃ እንደሚያሳየው ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በ2023 የ7.9 በመቶ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን በተያዘው ዓመት የኢራን የነዳጅ ገቢዋም በ9 ወራት ውስጥ 34 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ሀገሪቷ በቀን ከ3 ሚሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ነዳጅን ታመርታለች።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች "ክስተቱ የተወሳሰበ እንዲሁም በጂኦፖለቲካዊ እና በሰብአዊ ቀውሶች ላይ የሚፈጥረው አንድምታ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በመካከለኛው ምስራቅ በስፋት የተስፋፋው ግጭት የኃይል ዋጋ እንዲጨምር እና የማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ንረትን ለማውረድ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሊገቱ ይችላሉ በሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2022 ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት ምዕራባውያን ሀገራት ከዓለም ዋና ዘይት ላኪዎች አንዷ በሆነችው ሩሲያ ላይ ማዕቀብ በመጣላቸው የተነሳ የነዳጅ ዋጋ በበርሚል ወደ 120 ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ ይታወሳል፡፡
የነዳጅ እና የኢነርጂ ዋጋ ላለፉት ሁለት ዓመታት ጭማሪ ማሳየቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚታየው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ዋነኛ መንስኤ ነው።ተንታኞች እስራኤል ለጥቃቱ የምትሰጠው ምላሽ በቀጣዮቹ ቀናት እና ሳምንታት የዓለም የገበያ ስርአት አሁን ካለበት ሁኔታ ሊቀይር የሚችል ይሆናል ብለዋል፡፡












