፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መጋቢት 30፣ 2016| NBC ETHIOPIA-ረመዳን በእስልምና ታሪክ በርካታ ታላላቅ ሁነቶች የተስተናገዱበት ታላቅ ወር ነው፡፡
ወሩ ከሌሎች የአረብኛ አስራ አንድ ወራት በተለየ ልዩ ስፍራ እንዲያገኝ ያስቻሉት የተለያዩ ሁነቶች ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል የቁርዓን በዚህ ወር ውስጥ መውረድ ዋነኛው ነው፡፡

የእስልምና እምነት መመሪያ የሆነው ቁርዓን በነብዩ ሙሃመድ ላይ በ23 አመታት ውስጥ ተከታትሎ ሲወርድ መጀመሪያ መውረድ የጀመረው በዚሁ የረመዳን ወር ውስጥ ነው፡፡
በተጨማሪም በአንዲት ሌሊት አምልኮ የአንድ ሺህ ወር ምንዳ የሚገኝባት ለይለተል ቀድር የተሰኘችዋ ሌሊት መገኛዋ በዚህ ወር ውስጥ መሆኑ ደግሞ ሌላው የወሩን ታላቅነት አመላካች አንደሆነ የእምነቱ መምህራን ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ እውነታዎች ባሻገር ይህንን ወር የሚያልቁና በረመዳን ወር አሁን ድረስ የሚታወሱ በርከት ያሉ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡
ከነዚህም መካከል የበድር ዘመቻ ቀዳሚው ነው፡፡
የበድር ጦርነት ነብዩ ሙሃመድ ወደ መዲና ከተሰደዱ በሁለተኛው አመት የተደረገ ሲሆን ይህም በረመዳን አስራ ሰባተኛው ቀን የተከሰተ ጉልህ ሁነት ነው፡፡
የመካ ባለ ስልጣናት ከመዲና የሚመጡ ሙስሊሞች ኡምራ እንዳያደርጉ መከልከላቸው፣ ነብዩን ተከትለው ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለስቃይ እና እንግልት መዳረጋቸው እንዲሁም በመዲና የሚገኙ አይሁዶችን በማነሳሳት በከተማዋ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመፍጠር የተቻላቸወን ሲያደርጉ መቆየታቸው ለዚህ ጦርነት መነሻ እንደነበር ይነገራል፡፡
ለጦርነቱ መነሻ የሆኑት እነዚህ ምክንያቶች በእስልምና ሀይማኖት እንዳይካሄድ ክልክል የነበረውን ጦርነት ሽሮ በሙስሊሞችና በቁረይሾች መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ጦርነት ሆነ፡፡
በወቅቱ ከነብዩ ሙሃመድ ጋር የነበሩ አማኞች ቁጥር እጅግ አናሳ የነበረ ቢሆንም እነርሱን ለመርዳት መልዓክት ከሰማይ መውረዳቸውን የእስልምና እምነት መምህራን ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ጦርነትም በነብዩ ሙሃመድና ተከታዮቻቸው ላይ ከፍተኛ ግፍ ሲፈጽም የነበረው አቡጀህል ተገደለ፡፡
ይህም ጦርነት ሙስሊሞች በቁረይሾች ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው የጦር ሜዳ ድል በዚሁ የረመዳን ወር የተመዘገበ ነበር፡፡
ሌላኛው በዚህ ረመዳን ወር ውስጥ ከተሰከሰቱ ሁነቶች ውስጥ የመካ መከፈት ተጠቃሽ ነው፡፡

ነብዩ ሙሃመድ ነብይነትን ከተቀበሉ በኋላ ቁረይሾች በእርሳቸውና በተከታዮቻቸው ላይ በርካታ በደሎችን ያደርሱ ነበር፡፡
በቁረይሾች የሚደርስባቸውን እንግልት መቋቋም የተሳናቸው ነብዩ ሙሃመድ ተከታዮቻቸውን ወደ ሀበሻ ሸኝተው እርሳቸው ደግሞ የተወለዱባት መካ ከተማን ትተው ከአቡበክር ሲዲቅ ጋር ወደ መዲና ተሰደዱ፡፡
መዲና ውስጥ በቆዩባቸው አመታት ከቁረይሾች ጋር ሁደይብያ የተሰኘ ስምምነት ላይ ቢደርሱም ቁረይሾች ስምምነቱን ማፍረሳቸውን ተከትሎ ነብዩ ሙሃመድ መካን ለመክፈት ጉዞ አደረጉ፡፡
ከመካ ከወጡ በስምንተኛው አመትም አስር ሺህ ወታደሮችን በማስከተል መካን ያለ ምንም ደም መፋሰስ መክፈት የቻሉት በዚሁ በታላቁ የረመዳን ወር ውስጥ ነበር፡፡
ከነብዩ ሙሃመድ ጋር ለ23 አመታት በትዳር የቆዩትና የመጀመሪያ ባለቤታቸው የነበሩት ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት በዚሁ በረመዳን ወር ውስጥ ነው፡፡
ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ ነብዩ ሙሃመድ ነብይ ሆነው ሲላኩ ነብይነታቸውን ተቀብለው የተከተሉ የመጀመሪያዋ እንስትም ናቸው፡፡
ነብዩ ሙሃመድ ከነበሯቸው ሰባት ልጆች መካከል ስድስቶቹ ከኸዲጃ ያገኟቸው ሲሆን እርሳቸውን በሞት እስኪያጡ ድረስ ሌላ ሚስት አላገቡም፡፡

ነብዩ ሙሃመድ ባለቤታቸውን ኸዲጃ በሞት ካጡ ብዙም ሳይቆይ በዛው የረመዳን ወር ውስጥ አጎታቸውን አቡ ጣሊብን በሞት ተነጠቁ፡፡
አመቱም የሀዘን አመት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህም በረመዳን ወር ተከስተው ካለፉ ክስተቶች መካከል ነው፡፡
በወቅቱ አስፈሪ ጦር የሚባሉት ሞንጎሊያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት የገጠማቸው በዚሁ በረመዳን ወር ውስጥ በተደረገ ጦርነት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡
ሽንፈት ገጥሞት የማያውቀው የሞንጎሊያ ኢምፓየር በእስልምና ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የተጀመረው ውጊያ የመጀመሪያው የሞንጎሊያውያን ሽንፈት ሆኗል፡፡
በውጤቱም በሞንጎሊያውያን ጦር እጅ ሊወድቅ የነበረውን ኢስላማዊ ግዛትን ማዳን ከመቻሉም በተጨማሪ የሞንጎሊያን ግዛት ወደ ምዕራብ ከመስፋፋት አግዷል፡፡
በታላቁ ረመዳን ወር ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎችም ሁነቶች ተመዝግበው አልፈዋል፡፡












