፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መጋቢት 20፣ 2016| NBC ETHIOPIA-የተወለደው እ.ኤ.አ በሚያዝያ 7 1954 በቻይና በሆንግ ኮንግ ነው፡፡ ተዋናይ፣ ዳይሬክተር፣ ደራሲ ፣ ሥራ ፈጣሪ ፣ ሙዚቀኛ ፕሮዲዩሰር እንዲሁም የማርሻል አርቲስት እና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ጃኪ ቻን ወደ ፊልም ኢንደስትሪ ከመግባቱ በፊት ‹‹በፔኪንግ ኦፔራ›› ት/ቤት በቻይና ድራማ አካዳሚ የትወና ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ከትወና ትምህርት ጎን ለጎንም የአክሮባትቲክስ እና ማርሻል አርት ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡ እነዚህ ተጨማሪ ክህሎቶች በፊልሙ አለም አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲያካትት እድልን ሰጥቶታል፡፡ ቻን ወደ ትወናው የተቀላቀለው በ1960 በአምስት ዓመቱ ሲሆን፣ 1962 ደግሞ ቢግ ኤንድ ሊትል ዎንግ ቲን ባር(Big and Little Wong Tin Bar ) የተሰኘ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡
የአክሽን እና ኮሜዲ ይዘት ያለው Snake in the Eagle’s Shadow የተሰኘው ፊልም ለቻን እውቅና እና ተወዳጅነት ያገኝበት ስራው ነበር፡፡ ፊልሙ 1 ሰአት ከ38 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 1978 ዓ.ም ነበር ለእይታ የቀረበው፡፡
ፖሊስ ስቶሪ የተሰኘው ፊልም በ1985 በሆንግ ኮንግ ከተማ የተሰራ ሲሆን፣ ጃኪ ቻን ዋና ገጸ ባይሪውን በመወከል እንዲሁም የፊልሙ ዳይሬክተር በመሆን ተሳትፏል፡፡ ፊልሙ በ1988 ፖሊስ ስቶሪ 2 እና በ2004 ኒው ፖሊስ ስቶሪ የሚባባሉ በ2 ተከታታይ ክፍሎች የቀረበ ነው፡፡
ሌላኛው ጃኪ ቻን ተወዳጅነትን ያተረፈበት ፊልሙ ድራንከር ማስተር የተሰኘው ፊልም ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 1978 የማርሻ አርት ስልጠናን በመውሰድ ውስጥ ያሉ ትግሎችን እና ፈተናዎችን ቁልጭ ድርጎ የሚያሳይ ታሪክ አዝሏል፡፡ የፊልሙ 2ተኛ ክፍል ከዓመታት በኋላ ድራንከር ማስተር 2 በሚል ለተመልካቾች ደርሷል፡፡

የRush Hour ተከታታይ የኮሜዲ እና አክሽን ዘውግ ያለው፣ ሲሆን ጃኪ ቻን እና ከክሪስ ታከር ጋር በመሪነት የተወኑበት ፊልም ሲሆን ለጃኪ ይበልጥ ስሙን እና ተወዳጅነቱን ከፍ ያደረገለት ፊልም ነበር፡፡ ፊልሙ 3 ተከታተይ ክፍሎች ይዞም ዘልቋል፡፡
በዓለም ላይ ታዋቂው እና ተወዳጁ ቻን በሆንግ ኮንግ እና በሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ዝናን እና የተለያዩ ሽልማትን መጎናጸፍ የቻለ ድንቅ ተዋናይ ነው፡፡ ከአክሽን ፊልሙ ኢንዱስትሪ ባለፈ ቻን በተለያዩ የፖፕ ዘፈኖች፣ የካርቶን ፊልሞች እና የቪዲዮ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ ፎርብስ መጽሄት በዓለም ላይ ዝነኛ የሆኑና እና የተቸገሩ ሰዎችን ከሚረዱ 10 ሰዎች መካካል ጃኪ ቻንን አንዱ እንደሆነ አስነብቦ ነበር፡፡ ስለ ቻን ብቃት በርካቶች ምስክርነት የሰጡ ሲሆን የፊልም ምሁሩ አንድሪው ዊሊስ ቻን ጃኪ ቻን “በዓለም ላይ በጣም ታዋቂው የፊልም ተዋናይ” እንደሆነ መስክሮለታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የሀብት መጠኑ 350 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን እና በ2016 በዓለም ላይ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ተዋናይ እንደነበርም ፎርብስ በመጽሄቱ አስነብቧል።
ቻን እ.ኤ.አ በ2016 የኦስካር ሽልማትን ጨምሮ ከ30 በላይ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ጃኪ ቻን ላላፉት 7አስርት አመታት በቻይና የፊልም አለም በሀገር ውስጥ ፊልም አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ፊልሞችን በመስራት፣ የተለያዩ የፊልም ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ከዛን ባለፈ የቻይና ፊልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ እና ተመራጭ እንዲሆን የበኩል አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 በቻይና፣ህንድ፣ አየርላንድ እና የተባቡት አረብ ኤምሬትስ ሀገራት ቀረጻው የተካሄደው ኩንግ ፉ ዮጋ ፊልም ከፍተኛ ገቢ ያስገኘ ፊልሙ ሆኗል። ከ258 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2023 የተሰራው Teenage Mutant Ninja Turtles ጃኪ ቻን በእርጅና እድሜው ላይ ሆኖ ድንቅ ብቃቱን ያሳየበት የአኒሜሽን ፊልም ነው፡፡
ጃኪ ቻን ፕሮጀክት ኤ፣ ዘ ፎሬን፣ራምብል ኢን ዘ ብሮንክስ፣ ኩንግ ፉ ፓንዳ፣ The Spy Next Door፣ Bleeding Steel ፣The Karate Kid TheForbidden Kingdom፣ ጨምሮ እ.ኤ.አ እስከ 2021 ድረስ በ 200 ፊልሞች ላይ መተወን የቻለ ድንቅ ተዋናይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ቻን የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ (ሲሲፒ) ፖለቲከኛ ሆኖ ለሁለት ጊዜያት የቻይና ህዝቦች የፖለቲካ አማካሪ ኮንፈረንስ ተወካይ በመሆን አገልግሏል፡፡
የ69 አመቱ ኮከብ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲቀርብ እርጅና ተጫጭኖት ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ አድናቂዎቹ “ጀግናችን አላረጀም” የሚሉ የስስት ሀሳቦችን ሲያንጸባርቁ ተስተውለዋል፡፡ በብዙዎች የፊልም አፍቃሪያን ዘንድ አይረሴው ቻን በቻይና የፊልም እንዱስትሪ የማይናወጥ አሻራውንን ከማኖሩ ባሻገር በዓለም መድረክም ስሙን ገናና ማድረግ ችሏል፡፡ ይህ እውቅ አርቲስት የፊታችን ሚያዝያ 7 70ኛ ዐመት ልደቱን ያከብራል።
በ-ሀሴት ኃይሉ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












