አዲስ አበባ | መጋቢት 19፣ 2016| NBC ETHIOPIA-የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት፣ የአርሰናል ተከላካይ ቤን ዋይት ከ2024 የአውሮፓ ዋንጫ በፊት ወደ ስብስባቸው የመመለስ ፍላጎት ካለው “አሁንም በራችን ክፍት ነው” ብለዋል።
የ26 ዓመቱ መድፈኛ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም በሚል ምክንያት ከብራዚልና ቤልጅየም ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ካደረገው የሶስቱ አናብስት ስብስብ ውጭ እንደነበር ይታወሳል።
የእርሱ አለመኖር በጉዳት እየታመሰ የሚገኘውን የጋሬዝ ሳውዝጌት የኋላ መስመር ይበልጥ ለችግር ዳርጓል።

የሶስቱ አናብስት አለቃ ሳውዝጌት ለጋዜጠኞች፣ “ቀደም ብየ እንደተናገርኩት አሁንም በራችን ለቤን ክፍት ነው። ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታዎች የተጫወቱ ተጨዋቾች እያሉ አንድም ያልተጫወተውን ቤን ዋይትን መምረጥ ከባድ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም አራት ተጨዋቾቻችንን በጉዳት በማጣታችን የእርሱ መመለስ በብዙ ያስፈልገናል” ብለዋቸዋል።
ኬራን ትሪፔር፣ ሪስ ጄምስ፣ ሉክ ሾው፣ ማርክ ጊሂ እና አሌካሳንደር አርኖልድ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጭ ያሉ ተጨዋቾች ሲሆኑ ካይል ዎከርና ጆን ስቶንስ ደግሞ ከብራዚልና ቤልጂየም ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ጉዳት አጋጥሟቸው ለማቋረጥ መገደዳቸው ይታወሳል።
ቤን ዋይት በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የወንበር አሟቂነት ሚናውን መታገስ ባለመቻሉና ከምክትል አሰልጣኙ ስቲቭ ሆላንድ ጋር በገቡብት እሰጥ አገባ ምክንያት በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ካምፕ ጥሎ ከወጣ በኋላ አንዴም በሶስቱ አናብስት መለያ አልታየም።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












