፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መጋቢት 17፣ 2016| NBC ETHIOPIA -በጥንታዊነቷ በምትታወቀው በጣሊያን ግዛት ውስጥ የምትገኝው የፓትሪካ ከተማ ከሰሞኑን ለሃገሬው ነዋሪ ይዛው የመጣችው አማራጭ ሃሳብ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የኑሮ ውድነት ጣሪያ በነካበት ከዕለት ጉርስ ባሻገር መሰረታዊ ነገር ቅንጡ በሆነበት በዚህ ዘመን ይህች የጣሊያኗ ፓትሪካ ግን ባዶ ቤቶቿን በአንድ ዩሮ ለከተሜው ነዋሪ ለመቸብቸብ ልመና ውስጥ እንደሆነች ለሲኤን ኤን ሹክ ብላለች፡፡
ከተማዋ ከሮም በስተደቡብ ምስራቅ 70 ኪሎ ሜትር እና ከፍሮሲኖን በስተደቡብ ምዕራብ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከፍ ባለ ኮረብታ፤ ሸለቆ እና ተራራሮች አቅራቢያ የምትገኘው ፓትሪካ ጁሊያኖ ዲ ሮማ እና ሱፒኖን የተባሉ አዋሳኝ ከተሞችም አሏት፡፡ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብዙ ነዋሪዎች ከፓትሪካ ወደ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢንዱስትሪ ስራዎች መፍለሳቸው ይነገራል፡፡ ይህን ተከትሎ ከተማዋ አነስተኛ የህዝብ ቁጥር እንዲኖራት ምክንያትም እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ በጥቂቱ ስለ ፓትሪካ ይህን ካልን ዛሬ ላይ ከተማዋን አነጋጋሪ ወዳደረገው ጉዳያችን እንዝለቅ፡፡
ከ3ሺ ያልዘለለ ነዋሪዎችን ያቀፈችው ፓትሪካ ከ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እጣ ፋንታቸውን ለኦና በረሃ የሰጡ ከ40 በላይ የሚሆኑ ቤቶች ይገኙባት ነበር፡፡ በርካቶች ቤታቸውን ባዶ ትተው ለአስርት አመታት ወደ ሌላ ቦታ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ መሄዳቸው ለከተማይቱ ጭርታ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ከተማውን ዝም አሰኝተውታል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከ100 ዓመታት በላይ ባለቤት አልባ ሆነው የቆዩ ቤቶች ስለመኖራቸው መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

በዚህ ከቀጠለ የከተማይቱ ተስፋ መቶ በመቶ እንዳያከትም የሰጉት የመንደሪቷ ገዢ መላን ለመዘየድ አንድ ቤት በአንድ ዩሮ ሲሉ ገበያን መክፈታቸው ተሰምቷል፡፡ እንደ መፍትሄም ለማስቀመጥ በመጀመሪያ የተተዉ ቤቶችን ሁሉ ካርታ አዘጋጅተው የቤቱን ባለቤቶች ንብረታቸውን እንዲረከቡ በይፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ሁለት ቤቶችን ብቻ ነው በአንድ ዩሮ ማሻሻጥ የቻሉት፡፡
ለዚህ አይነቱ ክስተት ፓትሪካ የመጀመሪያ ባትሆንም የሌሎች ከተሞች ልምዶችን ለመውሰድ ያደረገችው ጥረትም አልተሳካላትም፡፡ ከዚህ ቀደም ሌሎች ከተሞች ባዶ ቤታቸውን ለመሸጥ በሚል ገዥዎችን ለማግኘት የዘየዱት ዘዴ ነዋሪውን ለመመለስ መነሳሳትነ ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡ ለዚህ ያልታደለችው ፓትሪካ ግን ያስቀመጠችው መላ በርካቶችን ያጎርፋል ተብሎ ሲጠበቅ ገዢ መጥፋቱ ደግሞ ትኩረት ሳቢ ሆኗል፡፡
ፓትሪካን የገጠማት ሌላው ችግር ባዶ ቤቶችን ከመሸጡ በፊት ከዋናው ባለቤቶች በቀላሉ ፈቃድ ማግኘት አለመቻላቸው ነው። ሌላው ደግሞ ንብረት የሚካፈሉ ዘመዶች በግላዊ ጉዳዮች እርስ በርሳቸው ስለማይስማሙ ወይም በሽያጩ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ከቤቱ ይልቅ ፀቡ አይሎባች ሃሳቡን እግፍ አድርገውታል፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ፓትሪካን ለማነቃቃት የሚደረገው ጥረት አሁንም ቀጥሏል። የከተማው ማዘጋጃ ቤት የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በማሰብ የግብር እፎይታም እንካቹ እያለ ነው፡፡ ታሪካዊ ሕንፃዎችን ለማደስ እና ሥራ ፈጣሪነትን ለማበረታታት የተጀመሩ ጅምር ተስፋዎችም ታይተዋል፡፡ በርካታ አዳዲስ ንግዶች በአካባቢው ለመክፈት መታሰባቸውም ለማህበረሰቡ የተነገረ ብስራት ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሂደት ግን ማንንም ንቅንቅ አላደረገም፡፡ ሃገረ ገዢውም ልመናውን ተያይዞታል፡፡ ማብቂያው ያልታወቀለት ይህ ሒደት አነጋጋሪነቱን እየቀጠለ ነዋሪውም አሻፈረኝ እንዳለ የከተማው አስተዳዳሪም መፍትሄን ለማበጃጃት ውጥን ዕያወጣ እልባት አልባ ጉዞን ቀጥሏል፡፡
በ-ማህሌት ግርማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












