፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መጋቢት 13፣ 2016| NBC ETHIOPIA -አለም በዕየለቱ የሚያስገርሙ እና እጅን በአፍ የሚያስጭኑ አዳዲስ ክስተቶችን ታስተናግዳለች፡፡
ከሰሞኑ በአለም ዙሪያ የተሰሙ አነጋጋሪ እና አስገራሚ መረጃዎች ውስጥ የተወሰኑትን እናስቃኛችሁ፡፡
1.የመጀመሪያው አስገራሚ መረጃ ወደ ፈረንሳይ ይወስደናል፡፡ በፈረንሣይ የሚገኘው ኮፐርኒ ብራንድ የተሰኘው የፋሽን እቃወች አምራች ኩባንያ ከሰሞኑ አዲስ የሰራው ቦርሳ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡

በየአመቱ በሰዎች ዘንድ አነጋጋሪ የሆኑ ምርቶችን በማምረት የሚታወቀው ይሄ ተቋም በዚህ አመትም በአይነቱ ለየት ያለ እና የብዙዎችን ቀልብ የሳበ አዲስ ቦርሳ ይፋ አድርጎል።
Air Swipe የሚል ስያሜ የተሰጠው ይሄ ቦርሳ ከሌላው ቦርሳ ለየት የሚያደርገው በአለም ላይ ቀላል እና ጠንካራ ነው ከሚባለው ኤርጄል ከተሰኘው ንጥረ ነገር የተሰራ ነው ይለናል የኦዲቲ ሴንትራል መረጃ።
ይሄ ደመናማ መልክ ያለው ቦርሳ 99 ከመቶ አየር ሲሆን 1 ከመቶው ብቻ መስታወት ነው፡፡ በዚም የተነሳ 33 ግራም ብቻ በመመዘኑ የአለም ቀላሉ ቦርሳ ለመሆን ችሏል ።
2. ሌላኛው ከወደ አውስትራሊያ የተሰማው የአለም የጊነስ ወርልድ ሪከርድ የሰበረው የብሉ ቤሪ መረጃ ነው።
በኮሪንዲ ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ የኮስታ የእንጆሪ እርሻ ውስጥ ጣዕሙን ሳይቀንስ የበቀለው ይሄ የአለም ትልቁ ብሉቤሪ የኢተርና ዝርያ መሆኑ ተነግሯል ።

በፈርንጆቹ 2020 የጊነስ ወርልድ ሪከርድን ይዞ የነበረው ብሉ ቤሪ 16.2 ግራም ይመዝን ነበር፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ በቀለ የተባለው ይህ ብሉ ቤሪ 20.4 ግራም መመዘን ችሏል፡፡ በዚህም ከዚህ ቀደም ተይዞ የነበረውን የአለም ትልቁ ብሉ ቤሪ ሪከርደን በማሻሻል በያዝነው ሳምንት የአለም ትልቁ ብሉ ቤሪ በመሆን የጊነስ ወርልድ ሪከርድን መስበር ችሏል፡፡
3. በዚህ ሳምንት የአለም ክብረ ወሰንን የያዘው ሌላኛው ክስተት በቻይና ተሰራ የተባለው የአለም ትልቁ ፋኖስ ነው ።
ቻይናዊያ የፀደይ ወቅትን ምክንያት በማድረግ የተገነባው የአበባ ቅርጽ ያለው ፋኖስ ከባለ 8 ደርጃ ህንጻ ቁመት ጋር እኩል እንደሆነ ጊኒየስ ወርልድ በገጹ አስፍሮታል፡፡
ይህ ግዙፍ የፒዮኒ ፋኖስ 45 ሜትር ወደ ጎን የሚረዝም ሲሆን ርዝመት ፣24 ነጥብ 84 ሜትር ከፍታ እንዳለው ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም 40ሺ ኪሎግራም ክብደት እንዳለው ተገልጻል፡፡

በ200 የኪነ ህንጻ ባለሞያዎች የተሳተፉበት እና በባህላዊ መንገድ የተገነባው ይህ ፋኖስ በከተማዋ ታዋቂ በሆነው ፒዮኒ በተባለው አበባ ቅርጽ የተሰራ ሲሆን ሰርቶ ለማጠናቀቅም ያለማቋረጥ 17 ቀን እና ማታ ፈጅቷል፡፡ በውስጡም ከ53ሺ በላይ የብርሃን ምንጮች እንዳሉት ወርልድ ጊኒየስ ሪከርድ አስነብቧል፡፡
4. ሌላኛው ከወደ ሜሪላንድ የተሰማው አስገራሚ መረጃ ነው፡፡
አንድ ግለሰብ በአንድ ሱቅ ውስጥ በጸሃፊነት የሚሰራውን ሰው አምስት የሎተሪ ቁጥሮችን እንዲገምትለት ይጠይቀዋል፡፡ የሱቁ ጸሃፊም ሳያመነታ የተጠየቀውን ያደርጋል፡፡ ታዲያ አሌክስ በመባል የሚታወቀው ግለሰቡ የዛ የሱቅ ጸሃፊ የመረጠለት የሎተሪ እጣ ቁጥር 50ሺ ዶላር አሸናፊ እንዳደረገው ተነግሯል።

አሌክስ ብዙውን ጊዜ የሚጫወተው ፓወር ቦል እና ሜጋ ሚሊዮን የተባሉትን የእጣ ጨዋታወች ብቻ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሆኖም ጓደኛው ፒክ 5 የተሰኘውን ጨዋታ እንዲጫወት እንደገፋፋው ገልጻል፡፡ ታዲያ በዚህ ቅጽበት ነው አሌክስ በአጠገቡ በነበረ ሱቅ በማቅናት የሱቁን ጸሃፊ አምስቱን ቁጥሮች እንዲገምትለት ያደረገው፡፡ እድል የቀናው አሌክስ የተገመተው የሎተሪ ቁጥር 50ሺ ዶላር እንዲያሸንፍ አድርጎታል፡፡
በ-የአብስራ ብርሃኑ












