አዲስ አበባ | መጋቢት 12፣ 2016| NBC ETHIOPIA – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያዩ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ በፈቃዳቸው እንዲመልሱ አሳስቧል።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካጋጠመው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሰዱና ያልተገባ የገንዘብ እንቅስቃሴ ካከናወኑ ግለሰቦች መካከል ብዙዎች የተደረገላቸውን ጥሪ አክብረው የራሳቸው ያልሆነውን ገንዘብ ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች እየቀረቡ እየመለሱ መሆኑን ባንኩ ገልጿል።
እስካሁን ቀርበው ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችም እስከመጪው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ በመቅረብ ተመላሽ እንዲያደርጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠቅመው አላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦች ላይ ደረጃ በደረጃና በተከታታይ የተለያየ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚገደድም ንግድ ባንክ አስታውቋል::
ከታቀዱት ዋና ዋና እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት እንዳሉ እንዲታወቁልኝ ሲል ባንኩ ገልጿል:-
????ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ሥም ዝርዝር በየቅርንጫፎች እና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት ኣካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎችን እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡
????አሁንም ቀርበው የማይመልሱ ከሆነ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በድርጊቱ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ፎቶግራፋቸውን እና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልፁ መረጃዎች ባንኩ በመረጠው የብዙሀን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
???? ከተጠቀሱት እርምጃዎች ጎን ለጎንም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የወሰዱትን ገንዘብ እስከ ቅዳሜ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦችን ከፍትህ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣የፍትሐ ብሔርና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያደርግ ንግድ ባንክ አሳስቧል።












