አዲስ አበባ | የካቲት 26፣ 2016| NBC ETHIOPIA -ከዛሬ 46 አመት በፊት የካቲት 26 1970 ታሪክ ሲወሳ የካራማራ ጦርነት ከአድዋ በኋላ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በውጭ ወራሪ እንዳትደፈር ታላቅ ጀግንነት የታየበት እና እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበት ጦርነት ነው። ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሀምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ባለው ጊዜ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት አካሂደዋል፡፡ በግምት ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ የምስራቅ ጦር ግንባሮች ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሰውተዋል።

ሶማሊያ በ1952 ዓ.ም ከጣሊያንና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን ባገኘች ማግሥት የሀገሪቱ መሪዎች “ታላቋ ሶማሊያን እንገነባለን” የሚል ህልም ማለም ጀመሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በ1953 ዓ.ም የድንበር ላይ ትንኮሳ ጀምረው በ1956 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብድረሺ አሊ ሸርማርኬ እንዲሁም በ1969፣ በ1972 እና በ1973 ዓ.ም ደግሞ ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ (ሜጀር ጀኔራል) የሶማሊያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ እንዲገባና ወረራ እንዲፈፅም ሰራዊታቸውን አዘዙ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ ሰርጎ ገቦችን አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በማስገባት ፈንጅ በማፈንዳት፣ ድንገተኛና የደፈጣ ጥቃቶችን በመፈፀም እንዲሁም ባለስልጣናትንና ሰላማዊ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት መሰናክል ሆነው መቆየታቸውንም በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊ የሰው ኃይል፣ የትጥቅ፣ የስንቅ፣ የሥነ ልቦና ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፤ኢትዮጵያ ግን በውስጣዊ ችግሮች ከመወጠሯም ባሻገር በወቅቱ የነበራት የሰራዊት ቁጥርና ጥራት እንዲሁም የትጥቅ አቅርቦት እጅግ የተመናመነ እንደነበርም ነው የሚገለጸው፡፡

300ሺ የሚሆን ሕዝባዊ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ ለውጊያ የተሰለፈ ሲሆን ፤የኩባና የደቡብ የመን መንግሥታት ጦራቸውን ይዘው ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፋቸውም ይታወሳል፡፡ ሶቭየት ኅብረት በጀኔራል ፔትሮቭ የሚመሩ ወታደራዊ አማካሪዎቿን ለኢትዮጵያ ረዳት አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ መላኳንም ታሪክ ይዘክራል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












