አዲስ አበባ | የካቲት 22፣ 2016| NBC ETHIOPIA -ወደ አድዋ ለነፃነት በነጋሪት ጉሰማ ጦርነት ሲጠራ ከደቡብ ከምስራቅ ከምዕራብ እና ከሰሜን የአገሪቷ ክፍሎች ኢትዮጵያውያን ሆ ብለው ተነሱ፡፡ በጀነራሎች ከሚመራው የጣሊያን ጦር ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ጦር 12 በሚሆኑ የጦር አዛዦች ተመርቷል፡፡
ከ12ቱ የጦር መሪዎች መካከል የዐድዋ ጀግና፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ተወላጆች ከሆኑት የላስታ መሪዎች አንዱ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ በጀግና ስማቸው አባ መርከብ ይገኙበታል፡፡ ዋግ ሹም ጓንጉል ብሩ ታላቅ የጦር ሰውና ከዋግሹም ብሩ ገብረ መድህን ልጆች አንደኛው ነበሩ፡፡ ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጋር መልካም ግንኙነት በነበራቸው ጊዜ በ1881 ዓ.ም ጃንጥራር በሚል ማዕርግ የአምባሰል ገዢ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በእዚህ ማዕረግም እስከ ሰኔ 1887 ዓ.ም ድረስ ቆይተዋል፡፡
የዋግሹም ጓንጉል ብሩ አባት ዋግሹም ብሩ ገብረ መድህን በ1887 ከጣሊያኖች ጋር ሚስጢራዊ ግንኙነት አድርገዋል ተብለው ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ተጠርተው ከስልጣናቸው ተነስተው ታሰሩ፡፡ ልጃቸው ዋግ ሹም ጓንጉልም በዋግ ሹምነት ተተኩ፡፡
ዋግሹም ጓንጉል ብሩ በ1887 ዓ.ም ሠራዊታቸውን ወደ ትግራይ እንዲያንቀሳቅሱ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ታዘዋል፡፡ የጣሊያኖች ግንባር ቀደም ምንጮች እንደጠቆሙትም የዋግሹም ጓንጉል ጠብመንጃ የያዘና በሚገባ የታጠቀ የጦር ሠራዊት ብዛት ከ10 ሺህ እስከ 11 ሺህ ይደርስ ነበር፡፡
ተዋጊው የዋግሹም ጓንጉል ብሩ ጦር ሠራዊት ታህሳስ 7 ቀን 1887 ዓ.ም ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጦር ጎን በመሰለፍ በአምባላጌ ተራራ የጦር ውጊያ ላይ ታላቅ ጀብዱ ሠርቷል፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደው በዋናው የአድዋ ጦርነት ላይም ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ሠራዊታቸውን ከሌሎች ጀግኖች አርበኞች የጦር ጀኔራሎች ሠራዊት ጋር በማደባለቅ በጀኔራል አልቤርቶኔ ይመራ የነበረውን የጣሊያኖች የቀኝ ክንፍ ኃይለኛ ጦር በማርያም ሸዊቶ የጦር ግንባር በቆራጥነት በመዋጋት አሸንፈው ጀኔራሉን እንዲማረክ አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት የዋግሹም ጓንጉል ብሩ ሠራዊት ብቻውን ከ4 መቶ በላይ የጣሊያን ወታደሮችና ባለ ማዕረግ የጦር መሪዎችን /መኮንኖችን/ ማርኳል፡፡ ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ከንጉሠ ነገሥቱ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ከድል በኋላ ምርኮኞቹን ወደዋግ ሰቆጣ ይዘዋቸው ተጉዘዋል፡፡
ዋግሹም ጓንጉል ብሩ የጦር ሜዳ ጀግና መሆናቸው ከመታወቁም ባሻገር በአስተዳደርም ዝነኛ ፍርድ ዓዋቂ አንደነበሩ ይተረክላቸዋል፡፡ አባ መርከብ የወራሪው ጣሊያን ጀነራል አልበርቶኒን እና ሌሎችም በርካታ የጣሊያን ወታደሮችን በመማረክ ጭምር ለአድዋ ድል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለነፃነት ለሉዓላዊነት በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬም ድረስ ትውልድ እያመሰገናቸው ይኖራል፡፡ ታዲያ አባቶቻችን በደማቸው ያስረከቡንን ድንቅ አገር የፈሰሰው ደማቸው፤ የተከሰከሰው አጥንታቸው ተወቃሽ እንዳንሆን ማክብር፣ ማስከበርና ቀጣይነቱን ማረጋጋጥ የትውልዱ ግዴታ ነው፡፡
በ-ሔርሜላ ፈቃደ












