አዲስ አበባ | የካቲት 19፣ 2016| NBC ETHIOPIA -ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤት ያንኳኳው የሀገር ፍቅር ስሜት ተሰናስሎ ዘመን የሚተርክለት፤ የዘመናዊ ኢትዮጵያ እርካብ የሆነውን አድዋን ወልዷል፡፡ በዚህ የመተባበር ድል የኢትዮጵያ ጦር በ12 የጦር አበጋዞች ተሰማርቶ ኢትዮጵያን ከጠላት ለመጠበቅ ደሙን ገብሯል፤ ጎኑን ተወግቷል፡፡
ለድሉ ቁልፍ የጦር መሪነት ሚናን ከተጫወቱ የወቅቱ ጦር መሪዎች መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ ጉርሙ አንዱ ናቸው፡፡ በፈረስ ስማቸው ጎራው በመባል የሚታወቁት ፊታውራሪ ገበየሁ ከአድዋ በፊት ከኢጣሊያ ጋር በተደረጉ የአምባላጌ እና የመቀሌ ጦርነቶች ለሀገራቸው በጀግንነት የተዋደቁ የጦር መሪም ናቸው፡፡
በአምባላጌ ጦርነት የጠላትን የጦር ሰፈር እንዲቃኙ በተላኩበት ጦርነቱን አስጀምረው፣ በስፍራው መሽጎ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ድል በማድረግ ምስራች አሰምተዋል፡፡ ለዚህ ተጋድሏቸውም የሚከተለው ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡-
“ያ ጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፤
ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው!!”
የወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦችም “የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና” በማለት እንዳወደሷቸው ተክለፃዲቅ መኩሪያ ፅፈዋል፡፡ የንጉሰ ነገስቱ የመሀል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረገው በሁሉም ጦርነት የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ፡፡ በመቀሌው ጦርነት በጀግንነት ተሳትፏቸው ሀገር ወዳድነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
የጦር አበጋዙ ተጋድሎ በአድዋ እጅጉን ደምቆ ተከትቧል ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምህረት በኩል የመጣውን እና በጄኔራል አልበርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበር፡፡ በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሰራዊቶቻቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው የትግል አውድማው በተፋፋመበት ውጊያ ፍልሚያ ገብተዋል፡፡ ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ ጠላትን ሲማርኩ፣ ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ፡፡
ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ አዲስ አበባ ድረስ ተማርኮ መጥቶ የነበረው የኢጣልያ መኰንን ጆቫኒ ቴዶኒ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በቢያን ኪኒና በማዘቶ በሚመሩት መድፎች እየተመቱ አበሾች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶ “ፈሪ እንዴት ትሸሻላችሁ? እኔ እንዴት እንደምሞት ለንጉሱ ሄዳችሁ ንገሩ!” በማለት ፈረሱን በአለንጋ አስነስቶ በግልቢያ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ›› ሲል ወኔውን በታሪክ ከትቦታል፡፡

ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ አድዋ ሲዘምቱ “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፤ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ!” ሲሉ ተናዘው እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በሕይወት እያሉ “የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፤ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” የተባለላቸው ፊታውራሪ ገበየሁ፤ አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አፅማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወስዷል፡፡ ከሰባት ዓመት በኋላም በትውልድ አካባቢያቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ-ክርስቲያን አፅማቸው አርፏል፡፡
በዘመናቸው ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ፊታዉራሪ ገበየሁ ደማቸውን ገብረው ሀገራቸውን በታላቅ ተጋድሎ ካከበሩ ጀግኖች መካከል አንዱ አድርጓቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ጉርሙ ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ ህይወታቸውን ገብረው ቢያልፉም በአድዋ ድል ዘመን አይሽሬ ስማቸውን ተክለዋል፡፡
በ-ሰላማዊት ወንደሰን












