አዲስ አበባ | የካቲት 18፣ 2016| NBC ETHIOPIA -የአደዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማህተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ በአደዋ ተራሮች የጀግንነት ታሪካቸውን በደማቅ አሻራ ከጻፉ ከአስራ ሁለቱ ዋነኛ የጦር አዛዦች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
“እንደ ደጋ ገብስ እንዲያ ኮስሶ
ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ
የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ!!”
ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፤ ደጃዝማች ባልቻ ሰፎ ሮባ አባ ነፍሶ በመባልም የሚታወቁት ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በአገምጃ ሶዶ ወይም አሁን ወሊሶ በተሰኘው ቦታ፣ በነሃሴ ወር 1854 ዓ.ም ተወለዱ። ገና ከልጅናታቸው ጀምሮ በምኒልክ ቤተ መንግስት የአጼ ምኒልክ የቅርብ አንጋች ሆነው በጦር ሞያ ተኮትኩተው አደጉ።
ደጃዝች ባልቻ የ36 አመት ጎልማሳና የሊቀ መኳስ አባተ አዛዥ በነበሩበት ወቅት ነው ወራሪው የጣልያን ጦር ባህር አቋርጦ ድንብር ሊጋፋ ማንነት ሊያጠፋ ከደጅ የደረሰው የካቲት 23 ፣1888 ዓ.ም የአድዋ ጦርነት ዕለት የጦሩ ዋና ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራው በጦርነቱ ላይ ሲሰዉ አጼ ምኒልክን ጨምሮ ብዙዎች እጅግ አዝነው ነበር፡፡
በዚህን ጊዜ ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ሆነ ህዝቡን ለማጽናናት፤ “ገበየሁ ቢሞትም ባልቻ አለልዎ” ለማለት እንደሚከተለው ተዘመረላቸው፡፡
“ገበይሁ ቢሞት፣ ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ”

ጀግናው ባልቻ የመድፍ ተኩስን ተምረው አጼ ምኒልክ ከፈረንሳይ አገር የተሰጣቸውን መድፎች በመተኮስ እና በማስተኮስ ስምና ዝናቸው ናኘ፡፡ በአደዋ ጦርነት ጊዜ፤ በመቀሌ፣ በአዲግራት እና በአድዋ ተራሮች መድፋቸውን ጠምደው፤የጣልያንን ጦር ከርቀት ድባቅ በምታት ጠላትን አርበድብደዋል፡፡
እንግዲህ የደጃዝማች ባልቻ የጀግንነት ታሪክ በተለይ ከአድዋ ድል በኋላ እየገነነ መጥቶ የመድፈኛ ክፍል ሃላፊ ከመሆን ጀምሮ፤ በኋላም በአጼ ምኒልክ ዘመን የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ሲቋቋም፤ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ደጃዝማቸ ባልቻ በእድሜ እና በእውቀት ሲጎለብቱ በመጀመሪያ ሲዳሞን ያስተዳደሩ ሲሆን ኋላም የራስ መኮንን የመጀመሪያ ልጅ ደጃች ይልማ ሲሞቱ፤ የሃረር ገዢ ሆነው ሐረርጌን እንዲያስተዳድሩ በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሹመዋል፡፡
በስተበኋላም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንጉሠ ነገሥትነቱን ዙፋን ሲይዙ፤ ባልቻ አባ ነፍሶን ከቀድሞ የአገር አስተዳዳሪነት ሹመት አንስተው ደጃች ብሩ ወልደገብርኤልን በመሾማቸው ደጃዝማች ባልቻ ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ስለመግባታቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና በ1929 ፈሺስት ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲወር፤በአደዋ ጦርነት ተሳትፈው በህይወት የቀሩ ብቸኛ የጦር አዛዥ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ! ነበሩ፡፡
ፋሽስት ጣሊያን ለዳግም ወረራ ኢትዮጵያን ሲረግጥ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጋር በነበራቸው ጸብ ምክንያት ንጉሠ ንገሥቱ ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ጄኔቭ ሲሄዱ፤ ደጃዝማች ባልቻ ከጣልያን ጎን ሊሰለፉ እንደሚችሉ ጣልያኖች ገምተው ነበር፡፡
ይሁንና ሁሌም ቢሆን በእናት ሀገራቸው ድርድር የማያውቁት ደጃዝማች ባልቻ ሰፎ ሮባ! በአደዋ ላይ የፈጸሙትን ጀብድ ሊደግሙ በ75 ዓመታቸው ጦራቸውን አሰባስበው ዳግም ከጠላት ጋር ሊተናነቁ ጎራዴያቸውን ሳሉ መድፋቸውንም ጠመዱ፡፡
የደጃዝማች ባልቻ ታሪክ በጣልያኖች ዘንድ ሲወራ ብዙዎችን አስገረመ። በወቅቱ የነበሩ የጣልያን ጋዜጦች በፊት ገጾቻቸው “በአድዋ ጦርነት ወቅት ከምኒልክ ጋር ሆኖ ከተዋጉት ሰዎች መካከል ባልቻ አባ ነፍሶ የሚባል የ75 አመት ሽማግሌ ሰው አሁን በህይወት አለ። በደቡብ በኩል ጦር እያደራጀ ነው።” የሚል ጹፍን ይዘው ወጡ፡፡
የጣልያን መንግስት፤ “ይህን ሰው እንፋረደዋለን። ከእነህይወቱ ይዛቹህ እንድታመጡት።” የሚል ትዕዛዝን አስተላለፈ።
በህይወት ዘመናቸው ጣልያንን ሁለት ጊዜ የተዋጉትና ብዙ ሺህ ተከታይ የነበራቸው ባልቻ አባ ነፍሶ የጣልያን ጦር ባደረሰባቸው ተከታታይ የአየር ድብደባ ብቻቸውን ቀሩ። በስተመጨረሻም የጣልያን ጦር ከበባቸው።
አንድ ነጭ ፈረንጅ ወደጃች ባልቻ ዘንድ በመምጣት “ደጃዝማች ባልቻ ማለት አንተ ነህ?” አላቸው። ደጃዝማቹም “አዎ እኔ ነኝ!” ሲሉ፤ ፈረንጁም “በሉ ይማረኩ። ሽጉጥዎትንም ያስረክቡኝ።” አላቸው። ደጃዝማች ባልቻም፤ “እኔ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም። ትጥቄንም አልፈታም !” ብለው ሽጉጣቸውን አውጥተው፤ ነጩን የጣልያን ጦር መኮንን ከገደሉት በኋላ ጥቅምት 27፣ 1929 ዓ.ም በራሳቸው ሽጉጥ የራሳቸውን ህይወት አጠፉ፡፡
ድንበር ተሻግሮ ሉዓላዊነታችንን ሊዳፈር የመጣን ጠላት በሁለት የጦርነት አውድ አንገት ለአንገት የተናነቁት ደጃዝማች ባልቻ ሰፎ ሮባ ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡ ፡ ክብር በደማቸው ሀገር ላቆዩልን ጀግኖች ይሁን!
በ-ጸጋሁን አሰፋ












