አዲስ አበባ | የካቲት 16፣ 2016| NBC ETHIOPIA -የጦርነት ታሪክ ፀሐፍት በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ አንዲት ሀገር በጦር ሜዳ አሸናፊ የምትሆነው በፍትሃዊ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ከሆነች ብቻ ነው። ጦርነቱ ፍትሃዊ ካልሆነ ግን መቼም ቢሆን አሸናፊ አትሆንም። ይህን እሳቤ ይዘን ወደ አድዋ ጦርነት ገፊ ምክንያቶች ስናመራ ኢትዮጵያ በዚያ ዘመን የገባችበት ጦርነት ፍትሃዊ ሆኖ እናገኘዋለን።
የኢትዮጵያ ጀግኖች በዚህ መርህ ተመስርተው ለሀገራቸው ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነት እና ክብር ሲሉ አድዋ ላይ ተዋድቀዋል፡፡ በአጼምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ አዝማችነት 12 ታላላቅ የማይበገሩ ጀግኖች ለአድዋ ድል መገኘት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡
ከእነዚህ የአድዋ አናብስትና አናብርት መካከል አንዱ ንጉስ ሚካኤል አሊ ሊበን ንጉሰ ወሎ ወትግሬ፤ አባ ሻንቆ ናቸው፡፡ ንጉስ ሚካኤል የደሴ ከተማ መስራች፤ የወሎው ባላባት፤ የልጅ እያሱ እና የወይዘሮ ስህን አባት፤ የአጼ ምኒልክ አማችና ቀኝ እጅ የሽዋ ረገድ ምኒልክ ባል፤ የእቴጌ መነን አያት፤ ወሎን 30 አመት ያስተዳደሩት የወረሂመኖ ባላባትና ገዥ ከነበሩት አሊ አባ ቡላ ከእናታቸው ገይቲ ገባቤ ጥር 27 ቀን1842 ዓ.ም ነበር የተወለዱት፡፡

“አባ ሻንቆ የአድዋው እንቆቆ
ጠላትን የሚጥል ሰይፍ ጋሻ አጥልቆ፤
የተንታው ግስላ የአባላጌው ነብር
ከጠላት መሀል ዘሎ የሚከመር፤
ንጉስ ሚካኤል ባለ ሶስት ግንባር
የወንዶች ቁና የማይደፈር”
ተብሎ የተገጠመላቸው ደፋርና የጦር አዝማች መሆናቸውን ራሳቸው ምኒልክ መስክረውላቸዋል፡፡ የወሎዉ ንጉሥ ራስ ሚካኤል በሶስቱም አዉደ ዉጊያዎች በመሳተፍ ታሪክ ሊዘነጋዉ የማይገባ ድል አድርገዋል፡፡ ራስ ሚካኤል አሊ ጠንካራ እና በቁጥር ብዙውን የጦር ሰራዊት በመገንባታቸው ይታወቃሉ፡፡
ከራስ ሚካኤል ጦር በቀር በሶስቱም አዉደ ዉጊያ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ጦር አለመኖሩ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ለዚህም ነዉ ራስ ሚካኤል በአድዋ ዘመቻ ግንባር ቀደም ከነበሩት ዘማቾች እና በአድዋ ጦርነት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ውስጥ አንዱ እንደሆኑ ታሪክ የሚዘክራቸው፡፡
የታሪክ ፀሀፍት እንደሚሉት የራስ ሚካኤል ጦር በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ቁጥሩ 70 ሺህ ደርሶ እንደነበር ፅፈዋል፡፡ ይህንን ጦር በጀግንነት በመምራት የአድዋ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በተለይም ራስ ሚካኤል በአድዋ ጦርነት የተጫወቱት ሚና ደማቁ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
ከአድዋ በፊት የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት አምባላጌ ላይ ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤልና የራስ መንገሻ ጥምር ጦር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተራራዉን ከቦ ከተዋጋ በኋላ የጣልያንን ጦር መሪ ሜጀር ቶሰሊን መግደል ችሏል፡፡ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ራስ ሚካኤል በአምባላጌዉ ጦርነት 15 ሺህ ጦር በማሰለፍ አኩሪ ታሪክ እንደሰሩ ፅፈዋል፡፡
በአድዋ ጦርነት ወቅት በጄኔራል ኦሬስቴ ባራቲየሪ ፊት አውራሪነት የተመራዉ የጣልያን ጦር ወረራ ያካሄደው በሶስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ወደ አደዋ የዘመቱትን የጦር አዝማቾችና ያዘመቱትን የሠራዊት ብዛት በተመለከተ ከንጉሠ ነገሥቱ በመቀጠል ሁለተኛ የሚባለዉን የሠራዊት ብዛት ይዘዉ የዘመቱት ራስ ሚካኤል እንደነበሩ ታሪክ መዝግቧል፡፡
ከወረኢሉ እስከ ትግራይ ድረስ በአጠቃላይ ለዘመተው ጦር ምግብ እና መጠጥ ያቀረበው የወሎ ህዝብ እና ንጉስ ሚካኤል አሊ ናቸው ይባላል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ የጣልያን ጦር የካቲት 22 ቀን ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ሊነጋጋ ሲል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አድዋ ጦር ግንባር ደረሰ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ታላቁ የአድዋ ጦርነት ተጀመረ፡፡
በዚህ ጦርነት በመካከለኛዉ ግንባር ራስ ሚካኤል ከትግል አጋሮቻቸዉ ጋር በመሆን ከጠላት ጦር ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀዉ በአሪሞንዲ የተመራዉን ጦር ድል ማድረጋቸውን እና የጣሊያኑን ጦር መሪ ጄኔራል አሪሞንዲም በዚሁ ጦርነት መሞቱን ታሪክ ያሳያል፡፡
የራስ ሚካኤል ሚና በዚህ የተገደበ አልነበረም፡፡ ከዳቦር ሚዳ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሲፋለም የነበረዉ የራስ አሉላ ጦር ከፍተኛ ጫና ላይ ስለነበር አፄ ምኒልክ የራስ ሚካኤል ጦር ወደስፍራዉ ሄዶ እንዲያግዝ ትዕዛዝ በሰጡበት ወቅትም ከዳቦር ሚዳ ተናንቆ የነበረዉን የራስ አሉላን ጦር ለማገዝ ወደ ግራ ግንባር ተንቀሳቀሰ፡፡ በዚህን ጊዜ ወታደሮቻቸው የሚከተለውን የፉከራ ዜማ አዜሙ፡፡
“ማን በነገረዉ ለጣሊያን ደርሶ
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ”
እንዲህ ባለ ሁኔታ የአሉላ እና የሚካኤል ጦር የጠላትን ጦር አሸንፎ ጄኔራሉን ዳቦር ሚዳን ገድሏል፡፡ ጥምር ጦሩ እኩለ ቀን ላይ ሙሉ በሙሉ የጣሊያንን ጦር ደመሰሰ፡፡ መሪዉን አልበርቶኔንም ማረከ፡፡ ጦርነቱ በግማሽ ቀን ዉስጥ በኢትዮጵያዉያን ድል አድራጊነት ሲጠቃለል ሀምሳ ስድስቱም የጣልያን መድፎች፣ በርካታ ከባድና ቀላል መትረየሶች እንዲሁም ጠመንጃዎች ተማርከዋል፡፡ ከእነዚህም ወስጥ በራስ ሚካኤል የተማረኩት በደሴ ሙዚዬም ይገኛሉ፡፡
ታሪኩ ብዙ ነው፤ ጀብዱ ተወርቶ አያልቅም፤ ዛሬ ንጉስ ሚካኤልን ስንዘክር ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀች፣ የራሷ ማንነት ያላት መሆኗንና የጥንት መሪዎች የመስዋዕትነት ታሪክ በውል መረዳት ግድ ይለናል፡፡ መረዳት ብቻ ሳይሆን በዛ ልክ ሠርቶ ሀገርን ማሻገር ግድ እንደሚል ነው፡፡ ክብርና ሞገስ ለወሎው ንጉሥ ራስ ሚካኤል አሊ ሊበን!!
በ-ቶማይ መካንን












