አዲስ አበባ | የካቲት 15፣ 2016| NBC ETHIOPIA -በቅኝ ግዛት ታሪክ አዲስ ክስተትን የፈጠረ፤ የማንአለብኝ ባዮቹን ምዕራባውያን አደብ ያስገዛ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች እና የጭቁኖች የነጻነት ምልክት የሆነ፤ በምዕራባውያን አይን እንደ ጨለማ ለተሳለችው አፍሪካ ብርሃን የሆናት፤ አድዋ፡፡

እምቢ ለሀገሬ ያለውን፤ ከሰሜን ከደቡብ ከምስራቅ ከምዕራብ ሆ ብሎ የተነሳው ህዝብ በአስራ ሁለት የጦር ክፍሎች ሲመደብ ይህን የአለም ታሪክ ቀያሪ ጦርነት ከመሩት የጦር መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው! ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፡፡
እንብዛም ታሪክ ካልዘከራቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል የሆኑት ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፤ በፈረስ ስማቸውአባ ገድብበህዝብ ዘንድ ተወዳጅና በነገስታቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ አርበኛ፣ የአስተዳደር ጥበብ አዋቂ፣ የንጉሰ ነገስቱ የቅርብ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ነበሩ፡፡
ስለ ትውልድ ዘመናቸው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት መወለዳቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም በወጣትነት ዘመናቸው ለውትድርና ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው አባታቸው ወደ ጎንደር ንጉሠ ነገስት አጼ ቴዎድሮስ ጋር ላኳቸው፡፡ በወቅቱ ወጣቱ ምኒልክም ከሸዋ መጥተው አፄ ቴዎድሮስ ጋር ስለነበሩ አንድ ላይ አደጉ፤ የውትድርና ሙያንም አብረው ተማሩ፡፡ በመቅደላ መድሃኒዓለም አምባ የአብነት ትምህርትን አብረው በመማራቸው ሳቢያ ወዳጅነታቸውና መተማመናቸው እጅጉን የጠነከረ ነበር፡፡
የአጼ ምኒልክ ስም ሲነሳ የራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ስም ሳይነሳ አይቀርም፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንግስናቸውን ሲይዙ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም አገርን የማቅናት ስራ ላይ በጦርነቱም በምክሩም ከጎናቸው አልተለዩም፡፡
ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የመተማ ጦርነትን ጨምሮ የሀገሪቱን ሉአላዊ ድንበር ለማስጠበቅ በተደረጉት ጥረቶች ሁሉ አሻራቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ ራስ ቢትወደድ መንገሻ በ1858 ዓ.ም የፊታውራሪነት፤ በ1881 የጃዝማችነት፤ በ1887 ዓ.ም ደግሞ የቢትወደድነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የራስነት ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡
በንጉሰ ነገስት አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ለመጀመርያ ጊዜ ራስ እና ቢትወደድነት የሚባሉት ማዕረጎች በአንድ ላይ የተሰጣቸው ግለሰብ እሳቸው መሆናቸውን የታሪክ መሁራን ያስረዳሉ፡፡
ቢትወደድ ማለት በልዩ ሁኔታ የተወደደ፤ ብቸኛ ወዳጅ ማለት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ራስ እና ቢትወደድነት የሚባሉት ማዕረጎች በአንድ ላይ የተሰጣቸው ግለሰብ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ናቸው፡፡ በንጉሰ ነገስት አጼ ምንሊክ ተወዳጅ መሆናቸው ማዕረጉን የማግኘታቸው ምክኒያት መሆኑ ይነገራል፡፡
አፄ ምኒልክ የራስ ቢትወደድነትን ማዕረግ ከሰጧቸው ከአንድ ዓመት በኋላ የአድዋው ጦርነት ተጀመረ፡፡ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከምም “የዳሞት እና የአገው ምድር ጦር” በሌላኛው መጠሪያው “የገበሬ ሰራዊት”ን እየመሩ የጠላት ሰራዊትን ሽንፈት አከናንቦ ወደመጣበት ለመመለስ ወደ አድዋ ዘመቱ፡፡
ጦራቸውን አሰባስበው ከአምባለጌ እስከ አድዋ ሶሎዳ ተራራ ያዋጉት ራስ ቢትወደድ መንገሻ 6 ሺ ሰራዊት የያዘው ጦራቸው ከራስ መኮንን እና ከዋግ ሹም ጓንጉል ጦር መካከል ሆኖ ለጠላት ሰራዊት ጀግንነቱን አሳይቷል፡፡
ለመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት ቀንዲል ከሆነው የአደዋ ድል በኋላ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ላሳዩት ጀግንነት ቡሬ ዳሞት ውስጥ ቡሬ አቦ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ መቀመጫቸውን አድርገው ተጨማሪ ግዛቶችን እንዲያስተዳድሩ አጼ ምኒልክ ሾሟቸው፡፡ በአስተዳደርነት ዘመናቸውም በርካታ ታላላቅ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል፡፡
በስተመጨረሻም ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም በሙሉ እንደራሴነት፣ በአፄ ምኒልክ ዋና አማካሪነትና ባለሟልነት ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው በ1903 ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ህይወታቸው አለፈ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን መፈጸሙን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ከጣሊያን የአምስት አመታት ዳግም ወረራ በኋላ ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለ ሥላሴ በጐጃም ክፍለ ሀገር ሁለት ትምህርት ቤቶችን ሲያስገነቡ አንደኛው በ1935 ዓ.ም በምዕራብ ጐጃም ዞን ቡሬ ከተማ የተገነባው በራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም የተሰየመው ትምህርት ቤት ነው፡፡
በ-መቅደስ ደምስ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv