አዲስ አበባ | ጥር 14፤ 2016| NBC ETHIOPIA – አሁን አሁን በመንገድ ላይ ስንሄድ በሚኒባስ ውስጥ የኩላሊት ታማሚዎች ተኝተው ሁለቱም ኩላሊቶቻቸው መስራት አቁመው ፤ በሳምንት 2-3 ጊዜ የኩላሊት እጥበት እየተደረገላቸው እንደሆነና ለዘላቂ መፍትሄ የውጪ ሀገር ህክምና እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ የገንዘብ እርዳታ መጠየቁን ከለመድነው ሰነባብተናል። ነገር ግን ስንቶቻችን ነን ስለ ኩላሊት እጥበት የምናውቀው?

የኩላሊት እጥበት ማለት ሁለቱም ኩላሊቶች ስራቸውን በአግባቡ ማከናውን ሳይችሉ ሲቀሩና መወገድ ያለባቸው መርዛማ ንጥረነገሮች ሳይወገዱ ቀርተው በደም ውስጥ በመጠራቀማቸው ጉዳት እንዳያደርሱ የሚወገዱበት፣ ወደሰውነት ተመልሰው መግባት ያለባቸው ንጥረነገሮች ደግሞ የሚመለሱበት እና የኩላሊትን የማጣራት ስራ በተወሰነ መልኩ የሚተካ የህክምና ዘዴ ነው።
የኩላሊት እጥበት ለሁሉም የኩላሊት ታካሚዎች ይደረጋል?

የኩላሊት እጥበት ለሁሉም የኩላሊት ታማሚዋች የማይደረግ ሲሆን የራሱ የሆነ የታማሚ የመመዘኛ መስፈርቶችም አሉት።
-የሰውነት የአሲድ መጠን መዛባት
-የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የሰውነት ክብደት ማሽቆልቆል
-ምንም አይነት የደም ስር ማግኘት ካልተቻለ
-ከፍተኛ የሆነ የልብ ድካም ካለ
-ደም ያለመርጋት ችግር ያለባቸው ሰዎች
-ከፍተኛ የሆነ የመርፌ ፍርሀት ካለ (Needle Phobia)
-በኩላሊት እጥበት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች
-የደም ግፊት መውረድ ወይም መጨመር
-የልብ ድካም እና የአመታት ስርአት መዛባት
-የጡንቻ ህመም
-አለርጂ (በእጥበቱ ወቅት ጥቅም ላይ ለሚውሉ ኬሚካሎች አለርጂ ሊያጋጥም ይችላል)
-ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት
-የራስ ምታት
-የነጭ የደም ህዋሳት ቁጥር መቀነስ
-የደም አርጊ ህዋሳት(platelets) ቁጥር መቀነስ እና መድማት
-ማሳከክ
-ከእጥበት በኋላ ድካም
-የማየት እና የመስማት ችግር
የኩላሊት እጥበት እስከ መቼ ይደረጋል?

የኩላሊት ህመሙ በድንገተኛ/ጊዜያዊ/ አሁናዊ የኩላሊት ጉዳት(Acute Kidney Injury) ለምሳሌ በመድሃኒቶች በሚከሰት የኩላሊት ጉዳት፣ በመርዝ( በእባብ በመነደፍ)፣ ወዘተ የመጣ ከሆነ እጥበቱ ጊዜያዊ እና ኩላሊት ወደቀደመ የስራ ብቃት እስኪመለስ ድረስ ብቻ ይሆናል።

ነገር ግን የቆየ የኩላሊት ህመም(Chronic Kidney Disease) ምክንያት ለምሳሌ በስኳር፣በደምግፊት፣በቤተሰብ በሚተላለፉ ወይም በዘረመል ላይ በሚፈጠር ችግር ምክንያት የሚደረግ እጥበት ከሆነ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስከሚደረግ ወይም እስከ ህልፈተህይወት ድረስ ዘላቂ ይሆናል።
የኩላሊት እጥበት ላይ ላለ ታካሚ ምን መደረግ አለበት?

የእጥበቱ ሂደት ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ያሉት፣ ረዥም፣አድካሚ እና አሰልቺ፣የእለት ተእለት እንቅስቃሴን ሊገድብ የሚችል እንዲሁም ውድ ከመሆኑ አንፃር ታካሚዎች የተስፋ መቁረጥ፣ የመበሳጨት፣ አለፍ ሲልም ህክምናውን ያለመቀጠል ስሜት ሊያሳዩ እንደሚችሉ ቀድሞ ማወቅ ፣ መዘጋጀትና አስታማሚዎች ለራሳቸውም ለታካሚዎችም ያልተቋረጠ የስነልቦና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪ የኩላሊት ንቅለ ተከላው ሊደረግ የሚችልበትን አማራጭ ማፈላለግም ሁነኛ መፍትሄ ነው።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












