አዲስ አበባ | ህዳር 05 2016| NBC ETHIOPIA -የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ገበያ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ስምምነት በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት እና ኢንደስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን መካከል ተደርጓል ።

የመግባቢያ ስምምነቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና አስፈላጊውንና ዘርፈ ብዙ የሎጀስቲክስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የሚኖሩ አምራቾች፤ አስመጪ እና ላኪዎች እንዲሁም በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚገኙ ባለሀብቶች የሚያስፈልጓቸውን የሎጀስቲክስ አገልግሎቶች በተመደቡ ሰራተኞችና ኃላፊዎች በነፃ ንግድ ቀጠናው እንዲያገኙ እንደሚያስችል ተገልጿል።
የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት አንዱ በመሆኑ የነፃ ንግድ ቀጠናው በማቀላጠፍ ቀጠናው ያለውን አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ስምምነቱ አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በማስቀረት፤ ጊዜን በመቆጠብና ከዚህ በፊት የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን የገቢ ወጪ ንግድና አገልግሎትን በማሳለጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በሰላማዊተ ወልደገሪማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












