አዲስ አበባ | ጥቅምት 13፤ 2016| NBC ETHIOPIA -በዓለም የታወቁና የተከበሩት የአለም ሎሪት ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው የሸዋ ነገሥታት ከተማ አንኮበር ላይ በዛሬዋ ቀን ጥቅምት 13 ቀን 1925 እ.ኤ.አ ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ።

ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ ሲወራት፣ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ፤ ከነጻነትም በኋላ አብይ ሥራ በወረራ የተበላሸችውን ሀገራቸውን እንደገና መገንባት እንደሆነ ነው። ለዚህም የሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶች ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።
በአሥራ አምስት ዓመታቸው እ.ኤ.አ 1940 ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ ሀገር ይላካሉ። ወጣቶቹ ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥቱን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ፣ አፈወርቅ ተክሌ ጃንሆይ የሰጧቸውን ምክር ሁሌም እንደሚያስታውሱት ይናገራሉ “ንጉሠ ነገሥቱ ተግታችሁ አጥኑ፣ ተማሩ ብለው ከመከሩን በኋላ ጠንክራችሁ መሥራት እና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ። ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ እንዴት ያሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ወይም መንገዶቻቸው የቱን ያህል ስፋት እንዳላቸው እንድትነግሩን አይደለም።” ነበር ያሏቸው።

አፈወርቅ ተክሌ በእንግሊዝ ሀገር የአዳሪ ተማሪ ቤትን ኑሮ ሲያስታውሱ የባዕድ ባህላት፣ የአየር ለውጥ እና የተለመደው የተማሪ ቤት ዝንጠላ እንዳስቸገራቸው ያወሳሉ። ቢሆንም ትምሕርታቸውን በትጋት ሲከታተሉ ቆይተዋል ። በተለይም በሒሣብ፣ በፖካርሲን (chemistry) እና በታሪክ ትምሕርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ሰለጠኑ። ነገር ግን አስተማሪዎቻቸው የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም።
በእነሱም አበረታችነት በእዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በሎንዶን የኪነ ጥበብ ማእከላዊ ትምሕርት ቤት (Central school of Arts & Crafts) ተመዝግበው ገቡ:: ተመረቁ። ትምሕርታቸውን አጠናቀው ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ የተከበሩ የዓለም ሎሪት ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ የኪነ ጥበብ ምሑር በየጥቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ፣ በየቦታው እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆዩ። “ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የሀገሬን ወግና ባሕል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል ነገር ግን በአፍሪካዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው።” ይሉ ነበር።
በሀያ ሁለት ዓመታቸውም እ.ኤ.አ 1946 ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን የኪነ ጥበብ ትርዒት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ። ወዲያውም ከዚህ ትርዒት ባገኙት ገቢ ተመልሰው ወደአውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ብሪታንያ እና ግሪክ ሀገሮች የጠለቀ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናወኑ። በተለይም በነኚህ ሀገሮች ውስጥ በስደት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቅ አጠኑ። እንዲሁም የመስታወት ስዕል (stained glass art) እና የ’ሞዜይክ’ አሠራርን ጥበብ ተምረው ወደሀገራቸው ተመለሱ።

በዚህ በሁለተኛ መልሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን በሃይማኖታዊ የግድግዳና ጣሪያ ስዕሎች፣ የ’ሞዜይክ’ ሥራዎች፣ መስኮቶቹንም በመስታወት ስዕሎች እንዲያሳምሩት ቀጥረዋቸው አሁን የምናያቸውን እንደ “የዳግማዊ ምጽአት ፍርድ”፣ የእመቤታችንን ንግሠት የሚያሳየው “ኪዳነ ምሕረት”፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት የሚያሳዩ ሥራዎቻቸው ይገኙበታል። አከታትለውም አሁን በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንንን ሀውልት ሠሩ። የስዕል እና ሌላ የኪን ሥራዎቻቸው ወዲያው በ’ቴምብሮች’፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበብ ትርዒት ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
የተከበሩ የአለም ሎሪት ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ/ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው፤ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዘህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv