አዲስ አበባ | መስከረም 22 2016| NBC ETHIOPIA- የአውሮፓ ሕብረት የተለያዩ የልማት መርሐ-ግብሮችን በማከናወንና በመደገፍ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፤ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።
በዛሬው እለትም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የሚደረገው የሕብረቱ የ650 ሚሊዮን ዩሮ የባለ ብዙ ዘርፍ ዓመታዊ የድጋፍ መርሐ-ግብርም የሁለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
የጉብኝቱ አላማ በ18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ፣ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እና ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ያሉት ኮሚሽነሯ የዚሁ ትብብር አካል የሆነው የ650 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ ዛሬ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን በቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ አመራሮችና ቀጣናዊ ልዑካን ጋር ይወያያሉ ተብሏል ሲል ኢዜአ በዘገባው ገልጿል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook- https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












