አዲስ አበባ | መስከረም 18 2016| NBC ETHIOPIA -የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ አባት ብፁዕ አቡነ ሰላማ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡

ብፁዕ አቡነ ሰላማ በቀድሞ ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሐረገ ወይን ገብረ ሥላሴ ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሥላሴ ገ/መድኅንና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ ወንድሙ በትግራይ ክፍለ ሀገር በመቀሌ ከተማ ልዩ ቦታው በዓታ ለማርያም በተባለው ቦታ 1934 ዓ.ም ተወለዱ።
ፊደልና ንባብና የቃል ትምሕርት በመማር ለግብረ ዲቁና የሚያበቃቸውን ትምሕርት ከየኔታ ክንፈ ገብርኤል በመማር ማዕረገ ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሰላማ በቀድሞ ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሐረገ ወይን ገብረ ሥላሴ ዜማ ከየኔታ ተክለ ማርቆስ ማየ አንበሳ ገዳም ተንቤን፤ ቅኔ ከየኔታ ንጉሤ መነዌ ገዳም ተንቤን እንዲሁም ቅኔን ከየኔታ አክሊሉ ደበጋ ጎንደር ትርጓሜ መጻሕፍት፣ እንድባ ጊዮርጊስ ከየኔታ ማርያም ቀረፃ ማርያም ከምትባል ገዳም ፤ ቅኔና ትርጓሜ መጽሐፍት እንድባ ጊዮርጊስ ከየኔታ ልሣነ ወርቅ ጎጃም ፤ ቅኔ ከየኔታ ዲበኩሉ ጎጃም በሚገባ ከተማሩ በኋላ ለመምህርነት በቅተዋል፡፡በተጨማሪም መዝገብ ቅዳን ከየኔታ ልዑል ቦረራ ሚካኤል ተምረዋል፡፡በወቅቱ የጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የቅስናና የቁምስና ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው የብፁዕነታቸውን ሽኝት መርሐ ግብር በተመለከተ በቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Telegram – https://t.me/nbcethiopiatv
Facebook- https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












