አዲስ አበባ | ጳጉሜ 1 2015| NBC ETHIOPIA-በእንግሊዝ መንግሥት ቫግነር የተሰኘው የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን አሸባሪ ተበሎ ሊፈረጅ ነው።

ይህ ህግ ከፀደቀ የቡድኑ አባል መሆን አሊያም ለቡድኑ ድጋፍ ማድረግ በእንግሊዝ በሕግ ያስቀጣል።ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ እንደሚጠቁመው የቡድን ንብረቶች የሽብርተኛ ቡድን ተብለው ይወረሳሉ።
የእንግሊዝ ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ቫግነር “አመፀኛ እና አጥፊ. . .የቭላድሚ ፑቲን ወታደራዊ መገልገያ ነው።”
ሚኒስትሯ ሱዌላ ብሬቭማን አክለው ቫግነር በዩክሬን እና በአህጉረ አፍሪካ የሚፈፅመው ድርጊት “ለዓለም አቀፍ ደኅንነት ስጋት ነው።”
“የቫግነር ቡድን አጥፊ ተግባራት ዋነኛ ጥቅሙ የክሬምሊንን ፖለቲካዊ አጀንዳ ከግብ ማድረስ ብቻ ነው። በቀላል እና አጭር ቋንቋ ሽብርተኛ ነው። አዲሱ የእንግሊዝ ሕግ ይህንን በግልፅ ያስቀምጣል” ብለዋል።
ቫግነር የተባለው ቅጥረኛ ቡድን ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። አልፎም በሶሪያ እና እንደ ሊቢያና ማሊ ባሉ የአፍሪካ ሃገራትም ተሰማርቷል።
የቡድኑ አባላት በዩክሬን ዜጎችን በመግደልና በማሰቃየት እንዲሁም በሌሎች በርካታ ወንጀሎች ይጠረጠራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2020 ዩናይትድ ስቴትስ የቫግነር ወታደሮች በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ፈንጅ ቀብረዋል ብላ ነበር።
የቡድን መሪ የቭገኒ ፕሪጎዢን በሩሲያ ከጥቂት ወራት በፊት በአጭሩ የተቀጨ ወታደራዊ አመፅ አንስተው ከከሸፈ በኋላ የቫግነር ዕጣ ፈንታ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2014 ቡድን የመሠረቱት ፕሪጎዢን ባለፈው ወር ከሌሎች የቫግነር ኃላፊዎች ጋር በአውሮፕላኑ እየበረሩ ሳለ ተከስክሰው መሞታቸው ተዘግቧል።
የቫግነር ስም እንደ ቦኮ ሐራም እና ሐማስ ካሉ ድርጅቶች እኩል በእንግሊዝ አሸባሪ የሚል መጠሪያ ይሰጠዋል።
የሽብርተኝነት ድርጊት 2000 የተሰኘው የእንግሊዝ ማዕቀፍ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር አንድን ድርጅት ሽብርተኛ ብለው እንዲፈርጁ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።

ሽብርተኛ የተባለወን ቡድን መርዳት አሊያም ከቡድኑ ጋር አብሮ መሥራት፣ ግንኙነት ማድረግና የቡድኑ ድርጊት እንዲቀጥል ማበረታታት፤ የቡድን ባንዲራም ሆነ ምልክት ማሳየት በሕግ የሚያስቀጣ ይሆናል።
ይህ ሕግ ተላልፈው የተገኙ ግለሰቦች እስከ 14 ዓመት የሚያደርስ እሥራት ወይም 5000 ፓውንድ ይቀጣሉ።
የእንግሊዝ መንግሥት ቡድኑን አሸባሪ እንዲለው ከፓርላማ አባላት ግፊት ይደርስበት የጀመረው ከወራት በፊት ነው።
የቫግነር ቡድን ባለፈው ሰኔ ከፈፀመው ወታደራዊ አመፅ በኋላ አልፎም የቡድኑ መሪ የአውሮፕላን አደጋ ነው በተባለ ክስተት ከሞቱ በኋላ መዳከሙ ይነገራል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት
#የአገልጋይነትቀን