አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 13/2015፣ NBC ETHIOPIA- የሻምፒዮናው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ከምሽቱ 3 ሰአት ከ55 ላይ 36 ሺህ ተመልካች በሚይዘው ‘National Athletics Centre’ ስታዲየም የሚደረገው የ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል።

በውድድሩ ላይ በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ ጉዳፍ ፀጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ለምለም ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
በትውልድ ኢትዮጵያዊት በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን፣ ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቺቤትና በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ካዛኪስታናዊ የሆነቸው አትሌት ካሮሊን ቼፕኮኤች ኪፕኪሩይ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 6 ሰአት ከ35 በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የማጣሪያ ውድድር የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለና አብርሃም ስሜ ይሳተፋሉ።
ከቀኑ 8 ሰአት ከ15 በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ አትሌት ብርቄ ኃየሎምና አትሌት ሂሩት መሻሻ ይሳተፋሉ።
ከምሽቱ 2 ሰአት ከ2 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያም እንዲሁ አትሌት አዲሱ ግርማ፣ አትሌት ታደሰ ለሚ እና አትሌት ሳሙኤል ዘለቀ ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ1 ሺህ 500፣ በ3 ሺህ መሰናክል፣ በ5 ሺህ፣ በ10 ሺህ ሜትርና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ800 ሜትር በሴቶች ብቻ እንደምትሳተፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
እስከ ነሐሴ 21/2015 በሚቆየው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ200 አገራት በላይ የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/