አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2 /2015 | NBC ETHIOPIA- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ እየሰጠ ይገኛል።

በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ያሉ መሆናቸው በግልፅ ይታወቃል፡፡
እነዚህን ልዩነቶችና አለመግባባቶች በንግግርና በምክክር መፍታት ሲገባ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ “የሀይል እርምጃዎች የኢትዮጵያን ደህንነትና ህልውና በመፈታተን ላይ መጥተዋል! ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት፣ በተለይም በሀረሪ፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ባለበት በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ተግባራት ለማከናወንና አጀንዳዎች ለመሰብሰብ በተዘጋጀበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ ተብሏል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ በመላው አገራችን የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል።
ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየትና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፡፡
በንጉሱ በቃሉ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc











