
አዲስ አበባ ሐምሌ 6 ፤ 2015 | NBC ETHIOPIA- ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ የተገነቡትን ከ 70 በላይ የመሸጫ ሱቆች የተካተቱበት የአቃቂ ሰብል ምርት ገበያ ማዕከልን እና በ140,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰፈረውን የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከል ከንቲባ አዳነች አቤቤ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝባችንን በብርቱ እየፈተነ ያለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከጀመርናቸው ስራዎች መካከል አንዱ የሆነው የሰብል ምርት ገበያ ማዕከል፣ ህብረተሰቡ በቀጥታ ከአምራቹ እንዲሸምት የሚያስችለው እና ገበያውን በማረጋጋት ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው ነው” ብለዋል።

የምርት ገበያው ሱቆችን ጨምሮ መጋዘን፣ ወፍጮ ቤት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት የተካተቱበት ሲሆን ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አምራቾች እና አርሶአደሮች የስራ እድል እንደሚፈጥር ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ጠቁመዋል።
የእንስሳት ልህቀት ማዕከሉ ደግሞ የዶሮና የወተት ላም እርባታ፣ የከብት ማደለብ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የምርት ማሳያና መሸጫ ቦታዎችን ያካተተ ነው።
ይህ የልህቀት ማዕከል በዘርፉ ለሚሰማሩ 485 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የእዉቀት፣ የክህሎት፣ የምርምር፣ የግብዓት፣ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫናዎች ለማቃለል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በታማኝነትና በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc